ቀጥታ፡

የግለሰቦችን የግል መረጃ ለታለመለት ዓላማ ብቻ ማዋል የሚያስችል የተጠናከረ የግል ዳታ ጥበቃ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2018 (ኢዜአ)፦ተቋማት የግለሰቦችን የግል መረጃ ለታለመለት ዓላማ ብቻ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ የሚያስችል የተጠናከረ የግል ዳታ ጥበቃ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ባልቻ ሬባ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 1321/2016 ትግበራና አፈጻጸምን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።


 

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ባልቻ ሬባ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ተቋሙ በህግ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ለግለሰቦች መረጃ የግል ዳታ ጥበቃ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዓለም ላይ እየታየ የመጣው ፈጣን የቴክኖሎጂ ዕድገት ለአዋጁ መውጣት ምክንያት መሆኑን ገልጸው፤ የግል መረጃዎች በአግባቡ ካልተያዙ ላልተፈለገ ዓላማ በመዋል የግለሰቦችን መብት እንዲጣስ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ አካል የሆነው የግል ዳታ ጥበቃ ሀገራዊ ፖሊሲ ለመቅረጽና ስትራቴጅ ለመንደፍ ግብዓት ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግረዋል።

ተቋማትም የግለሰቦችን ዳታ ህጋዊ እና ሃላፊነት በተሞላበት አግባብ መጠቀም እና መጠበቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የግለሰቦችን መረጃ ከታለመለት ዓላማ ውጭ የሚጠቀሙ ተቋማት ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር እንዳለ ገልጸው፤ ግለሰቦች የግል ዳታ ጥሰት ሲያጋጥማቸው ለተቆጣጣሪው አካል ሪፖርት የሚያደርጉበት ፖርታል ተዘጋጅቷል ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ተንታኝ ቤተልሔም መንግስቱ አየር መንገዱ በግል ዳታ ጥበቃ ዙሪያ የካበተ ልምድ እንዳለው ገልጸዋል።

በተቋሙ በየጊዜው በግል ዳታ ጥበቃ ማዕቀፉ ዙሪያ ለሰራተኞቹ ግንዛቤ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የህግና ፖሊሲ ዳይሬክተር ሳሙዔል ዓለሙ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ 42 ሚሊዮን ዜጎች ብሔራዊ ድጂታል መታወቂያ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።


 

በምዝገባ ወቅት ከግለሰቦች የሚወሰዱ ዳታዎች ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ እንዲውሉ ጥበቃ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የዋና ዳይሬክተር ልዩ አማካሪ ፍቅረ ሥላሴ ጌታቸው በበኩላቸው፤ የግል ዳታ ጥበቃ ለዲጂታል ሽግግር መሰረት መሆኑን አንስተዋል።


 

በግለሰቦችና ተቋማት መካከል መተማመን መፍጠር እንደሚያስችል አብራርተዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም