የመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጅ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊ ክብር ጋር ተጣጥሞ የተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጅ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊ ክብር ጋር ተጣጥሞ የተዘጋጀ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2018 (ኢዜአ)፡- የመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጅ ከኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት፣ ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊ ክብር ጋር ተጣጥሞ የተዘጋጀ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ ገለጹ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጅ ግብዓት የማሰባሰብ የባለድርሻ አካላት ውይይት አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ስመኝ ውቤ በሰጡት ማብራሪያ፤ ረቂቅ አዋጁ የህዝብና መንግስትን መተማመን የሚያጎለብት የመረጃ ተደራሽነትን እንደሚያሰፋ ገልጸዋል።
የመረጃ ነጻነት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ የቴክኖሎጂ ፈጣን ዕድገትና የመረጃ ነፃነትን የበለጠ ለማስፋት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
ረቂቅ አዋጁም ለመብትና ነፃነቶች መከበር፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ መልካም አስተዳደርና ሙስናን ለመከላከል ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጦች መመዝገባቸውና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕድገት ነባሩን አዋጅ ለማሻሻል ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በረቂቅ አዋጁም መረጃ የማግኘት መብት የሚገደብባቸው ልዩ ሁኔታዎች ከአፍሪካ ሞዴል የመረጃ ነፃነትና ዓለም አቀፍ ሕግጋት ጋር በማጣጣም በግልፅ እንዲቀመጥ መደረጉን አስረድተዋል።
መገናኛ ብዙኅን በአጭር ጊዜ መረጃዎችን በማሰባሰብ ለህዝብ በቀላሉ የሚያደርሱበትን የአሰራር ሥርዓት የሚያሳልጥ መሆኑን አብራርተዋል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ አስተያየት የሰጡት ባለድርሻ አካላትም፤ የመረጃ ነፃነት ከሀገር ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት ጋር የተገናዘበ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
በዚህም አዋጁ በረቂቅ ደረጃ መሻሻሉ የመረጃ ነፃነትን የበለጠ በማጠናከር የዲጂታል ሚዲያ ምኅዳሩን ተወዳዳሪነት በሚያበረታታ መልኩ መሆኑን ገልጸዋል።
ዋና ዕንባ ጠባቂ ስመኝ ውቤ በሰጡት ሃሳብ፤ ባለድርሻ አካላት የሰጧቸው አስተያየቶች የረቂቅ አዋጅ ዝግጅቱን በግብዓት የሚያጎለብቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በረቀቂ አዋጁ ላይ መረጃ ከተቋማት የሚሰጥበት ጊዜ ከ30 ወደ 21 ቀናት ዝቅ የተደረገ ሲሆን፤ አስቸኳይ መረጃም በ48 ሰዓታት እንዲሰጥ መመላከቱን ተናግረዋል።
የመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጁም ከባለድርሻ አካላት የተሰጡ ግብዓቶችን በማካተት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብ ይደረጋል ብለዋል።
በምክር ቤቱ የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ እንዳሉት፤ ረቂቅ አዋጁ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲሰጡና ኢትዮጵያ የደረሰችበትን ደረጃ በሚመጥን መልኩ የተሻሻለ ነው።
በቀጣይም ረቂቅ አዋጁን ለማዳበርና ለማጽድቅ ከባለድርሻ አካላት የሚነሱ ግብዓትና ሃሳቦችን በማካተት ለምክር ቤቱ መቅረብ እንደሚኖርበት አሳስበዋል።
የመረጃ ነጻነት ከሀገር ሰላምና ደኅንነት፣ ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊ ክብር ጋር ተጣጥሞ የተዘጋጀ መሆኑንም አስገንዝበዋል።