ቀጥታ፡

ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ተመለሱ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2018 (ኢዜአ)፡- የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ተመልሰዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ያጠናቀቁትን የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አሸኛኘት አድርገውላቸዋል።

ፕሬዚዳንት ማክሮን በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በሁለትዮሽ የትብብር ጉዳዮች ዙርያ ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።


 

የመሪዎቹን ውይይት ተከትሎም ኢትዮጵያና ፈረንሳይ የታዳሽ፣ የተቀናጀና ዘላቂ ኃይል እንዲሁም የዲጂታላይዜሽን ፕሮግራምን ለመተግበር የሚውል የ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት እንዲሁም የ150 ሜጋ ዋት የጂኦተርማል የመንግሥትና የግል አጋርነት አዲስ የማዕቀፍ እና የፍኖተ ካርታ ልውውጥ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከ125 ዓመታት በላይ ያስቆጠረና በጠንካራ የታሪክ መሰረት ላይ የተገነባ ነው፡፡

ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ግንኙነታቸውን ወደ ልዩ ስትራቴጂካዊ አጋርነትም አሳድገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጥቅምት 2011 ዓ.ም በፈረንሳይ ያደረጉትን ይፋዊ ጉብኝት ተከትሎ፣ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በአምስት ወራት ውስጥ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል፡፡

ፕሬዚዳንት ማክሮን የአሁኑ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ሦስተኛው ሲሆን ከዚህ ቀደም በመጋቢት 2011 ዓ.ም እና በታህሳስ 2017 ዓ.ም ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም