ቀጥታ፡

በህፃናት ላይ በትኩረት መስራት የወደፊት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መንገድ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2018 (ኢዜአ)፦ በህፃናት ላይ በትኩረት መስራት ድህነትን ለመቅረፍና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መንገድ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለፁ።

ላለፉት ሶስት ቀናት “አፍሪካ በቀዳማይ ልጅነት ስርዓት ለውጥ የግንባር ቀደምትነት ሚና፤ ከአካባቢያዊ ሞዴሎች ወደ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ” በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደው አዲስ ዓለም አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤ ተጠናቋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ  አቶ ጃንጥራር አባይ በጉባኤው ማጠናቀቂያ በህፃናት ላይ የሚደረግ መዋዕለ ንዋይ ድህነትን ለመቅረፍና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ቁልፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ጉባኤ በዘርፉ ያሉ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች የተለዋወጡበትና ለወደፊት ትብብር መሰረት የጣለ ነው ብለዋል።

ከተማዋ እያከናወነችው ያለው የኮሪደር ልማትና ሌሎች የልማት ስራዎች አዲስ አበባን ለህፃናት ተስማሚ እና ለሁሉም ተደራሽ የማድረግ ዓላማን የያዙ መሆናቸው ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን በየሁለት ዓመቱ በቋሚነት እንደምታዘጋጅ ገልጸው፤  ለጉባኤው ስኬታማነት አስተዋጽኦ ላደረጉ የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል እና ለሌሎች አጋር አካላትን አመስግነዋል።


 

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ  ዱጉማ በበኩላቸው፤ ጉባኤው መንግሥት አጋር ድርጅቶችና ማህበረሰቡ ለጋራ ዓላማ ሲቆሙ ለሕፃናት ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በተግባር የታየበት መድረክ ሆኗል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዘርፉ ያገኘችውን ውጤታማ ተሞክሮ ወደ ሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ለማስፋፋት መታቀዱንም ገልጸዋል።


 

አፍሪካ ያላትን ሀገር በቀል እውቀትና ተሞክሮ በመጠቀም ዓለም አቀፉን የቀዳማይ ልጅነት እድገት አጀንዳ የመምራት አቅም እንዳላት በጉባኤው አሳይታለች ብለዋል።

የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ከበደ ወርቁ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ጉባኤው አህጉራዊ አጋርነትን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ስኬት አስመዝግቧል።  


 

መድረኩ የአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ቋሚ አህጉራዊ የልምድ ልውውጥ ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግልና አፍሪካ በዘርፉ ያላትን ዓለም አቀፍ መሪነት የምታረጋግጥበት እንደሚሆን አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም