ቀጥታ፡

‎ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የስምንት አስርት ዓመታት ጉዞን ምክንያት በማድረግ ልዩ የመታሰቢያ ቴምብር ስብስብ አውጥታለች

‎አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የስምንት አስርት ዓመታት ጉዞን ምክንያት በማድረግ፣ "በሰላም አብሮ ለመኖር" በሚል መሪ ቃል ልዩ የመታሰቢያ ቴምብር ስብስብ ይፋ ማድረጓን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የስምንት አስርት ዓመታት ጉዞን ምክንያት በማድረግ "በሰላም አብሮ ለመኖር" በሚል መሪ ቃል ልዩ የመታሰቢያ ቴምብር ስብስብ ማውጣቷን በመልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል።


 

አራቱ ቴምብሮች እ.ኤ.አ. በ1945 በሳንፍራንሲስኮ የተባበሩት መንግሥታት ቻርተርን ከመፈረም ጀምሮ፣ በኮንጎ የሰላም አስከባሪ ኃይሎችን እስከ ማሰማራት እና በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደውን የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ማስተናገድን ጨምሮ የጋራ ታሪክን የሚተርኩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።


 

በዓለም የፖስታ ህብረት በኩል ለ192 ሀገራት የተሰራጩት እነዚህ ቴምብሮች፣ ለትውልድ ሁሉ የሚተርፍ የታሪክ ዐሻራ ማሳያ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና ለቡድናቸው፣ ሰላምን፣ ልማትን እና ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር እያሳዩት ላለው ጽኑ አመራር አድናቆታቸውን ገልጸዋል።


 

የተባበሩት መንግሥታት የጸናው ሀገራት ከመከፋፈል ይልቅ ውይይትን በመምረጣቸው መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያም ይህንኑ የሁልጊዜ ምርጫዋን እንደምታጸና አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም