ቀጥታ፡

የገጠር ኮሪደር ልማቱ የአርሶ አደሩን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው

ጎንደር፤ ግንቦት 5/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል እየተከናወነ ያለው የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥ መሆኑን የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ገለጸ። 

በጎንደር ከተማ አስተዳደር በሳይና ሳቢያ ገጠር ቀበሌ የተገነባው የገጠር ኮሪደር ልማት መንደር ዛሬ ተጎብኝቷል፡፡ 

በጠቅላላ ምርጫው ብልጽግና ፓርቲን በመወከል በጎንደር ከተማና ዙሪያ ገጠር ቀበሌዎች የሚወዳደሩ እጩዎች ትውውቅና ቅስቀሳ ተካሄዷል።


 

የቢሮው ኃላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በክልሉ እየተከናወነ ያለው የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥ ነው። 

በለውጡ ዓመታት መንግስት የአርሶ አደሩን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የግብርና ትራንስፎርሜሽንን በመተግበር ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል። 

የገጠር ኮሪደር ልማት ዘመናዊ ግብርናን በማስፋፋትና የአርሶ አደሩን የስራ ባህል ከፍ በማድረግ በኩል አዎንታዊ ሚና እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል። 

በጎንደር ከተማ ገጠር ቀበሌዎች የተተገበረው የገጠር ኮሪደር ልማት ለክልሉ ሞዴል መሆኑን ጠቁመው፤ ይህን መልካም ተሞክሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት ትኩረት ይደረጋል ብለዋል። 

ጎንደር በለውጡ ዓመታት ታሪኳንና የቀደመ ገናና ስሟን ሊመጥን የሚችል የልማት ተቋዳሽ ለመሆን በቅታለች ያሉት ደግሞ የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ናቸው። 

በከተማዋ በታቀፉ የገጠር ቀበሌዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮችን የልማቱ ተጠቃሚ በማድረግ በኩል መሠረተ ልማት የተሟላላቸው ሞዴል የገጠር ኮሪደር መንደሮችን መገንባት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡


 

የገጠር ኮሪደር መንደር ልማት አርሶ አደሩን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በማላመድ ወደ አዲስ ህይወት እንዲሸጋገር በር የከፈተ በመሆኑ የልማት ስራውን ወደ ሌሎች የገጠር ቀበሌዎች እንዲሰፋ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡  

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ስኬታማ እና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አርሶ አደሩ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል። 

የሳቢያ ሳይና ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሞገስ ተስፋሁን እንዳሉት፤ መንግስት በገጠሩ ክፍል የጀመራቸው የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ የአርሶ አደሩን የስራ ባህልና ተነሳሽነት ያሳደገ ነው፡፡

ልማቱ አርሶ አደሩ የነበረው አኗኗር ከመሰረቱ በመቀየር ምቹና ዘመናዊ ኑሮ እንዲመራ አዲስ ምዕራፍን የከፈተ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

መንግስት ግብርናው እንዲዘምን ባደረገው ያልተቆጠበ ድጋፍ አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል ያሉት አርሶ አደር ጌትነት ጫቅሉ ናቸው፡፡  

የሌማት ትሩፋትና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የአርሶ አደሩን የምግብ ሉዓላዊነት እያረጋገጠ ያለ ተግባር መሆኑን ነው ያመለከቱት። 

ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከመራጮች ምዝገባ  ጀምሮ በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመው የድምጽ መስጫውን  ቀኑን በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም