ማዕከሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በማላመድ በግብርና ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ እያገዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ማዕከሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በማላመድ በግብርና ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ እያገዘ ነው
ጂንካ፤ ግንቦት 5/2018(ኢዜአ)፡-የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በማላመድ በግብርና ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ማገዙን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አለማየሁ ባውዲ ገለጹ።
የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲና ሌሎች አመራሮች የማዕከሉን የሥራ እንቅስቃሴ ዛሬ ጎብኝተዋል።
በዚህ ወቅት አፈ ጉባኤው እንዳሉት፣ የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል የአርሶና የአርብቶ አደሩን ችግር የሚፈቱና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በማላመድ በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው።
ማዕከሉ በግብርናው ዘርፍ እያከናወነ ያለው የጥናትና ምርምር ሥራ በክልሉ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ላለው ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልጸዋል።
ማዕከሉ ያፈለቃቸውን የግብርና ቴክኖሎጂዎች ወደ አርሶና አርብቶ አደሩ በማውረድ ግብርናውን ለማዘመንና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትንም አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።
የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ወላይቴ ቢቶ በበኩላቸው፣ የምርምር ማዕከሉ ተግባር በተለይም በቆላማ አካባቢዎች በመስኖ ልማት የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እና የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በቆላማ አካባቢዎች በመስኖ ልማት የመጣውን ተጨባጭ ለውጥ በማስፋት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ማዕከሉ የጀመረውን እገዛ ሊያጠናክር ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዮት ሙላቴ (ዶ/ር) የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ በግብርና ዘርፍ ተጨባጭ ውጤት እንዲመዘገብ እያገዘ መሆኑን አንስተዋል።
በክልሉ ቀደም ሲል በሰብል ልማት በሄክታር ከ30 ኩንታል ያነሰ ምርት ይገኝ እንደነበር አስታውሰው፣ የምርምር ማዕከላት የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ማላመዳቸውን ተከትሎ በሄክታር ከ40 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት ተችሏል ብለዋል።
ለውጤቱ በአነስተኛ ቦታ ብዙ ምርት ማግኘት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ማድረግ መቻሉ ሌላው ምክንያት መሆኑንም ጠቅስዋል።
እንደ አብዮት (ዶ/ር) ገለጻ፣ ማዕከሉ የሩዝ ምርት ባልተለመደባቸው አካባቢዎች ጭምር የሩዝ ልማትን በማላመድና በማስፋፋት ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።
የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተርና የሰብል ተመራማሪ ተክሌ ዮሴፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው የምርምር ማዕከሉ የተጣለበትን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከማዕከሉ የሚወጡ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና የምርምር ውጤቶችን በአርሶና አርብቶ አደሩ ማሳ በማስፋት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደተቻለም አመልክተዋል።
ማዕከሉ በተለይም በዝናብ አጠር አካባቢዎች በመስኖ የሚለሙ እና ምርትን በእጥፍ የሚያሳድጉ የሰብል ዝርያዎችን እያላመደ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም በአርብቶ አደሩ አካባቢ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት ያግዛል ብለዋል ።