ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ፍትሐዊ ብቻም ሳይሆን በጋራ የመበልፀግ እሳቤን የያዘ ነው

ደብረ ብርሃን፤ ግንቦት 5/2018(ኢዜአ)፡-  የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ፍትሐዊ ብቻም ሳይሆን በጋራ የመበልፀግ እሳቤን የያዘ በመሆኑ ተገቢ የሆነ ምላሽን የሚሻ ነው ሲሉ ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የህልውና እና የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን ጥያቄው ተግባራዊ የሚሆንበት መንገድ ደግሞ በቀጣናው ሰላም እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ላይ የራሱ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዳለውም ምሁራኑ አንስተዋል።

ምሁራኑ አክለውም የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ፍትሐዊ ብቻም ሳይሆን በጋራ የመበልፀግ እሳቤን የያዘ በመሆኑ ተገቢ የሆነ ምላሽን የሚሻ ነው ብለዋል።


 

ከምሁራኑ መካከል  በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ ጌታቸው ከበደ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ዋና ማጠንጠኛ ከባህር በር፣ ከውሃና  ከወደብ ጋር የተቆራኝ ነው።

ተለዋዋጭ እየሆነ በመጣው የዓለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ለሁለንተናዊ እድገቷ የሚበጃትን የባህር በር ጥያቄ ማንሳቷ ተገቢነት ያለው መሆኑንም ነው ተመራማሪው የሚገልጹት።

እኛ ምሁራንም የባህር በር ጥያቄውን ፍትሃዊነት በታሪክ፣ በባህልና በሌሎች ሳይንሳዊ አመክንዮ ለማስረዳት መነሳሳት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

ለዚህም በጥናትና ምርምር ስራ ላይ በማተኮር የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄውን ተገቢነት ለአለም ህዝብ የማሳወቅ ስራ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።


 

የቀብሪ ደሃር ዩኒቨርሲቲ መምህርና የፌዚክስ ተመራማሪ መኩሪያ ፀጋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በተሳሳተ መንገድ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ መደረጉ ለከፋ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ  ችግሮች ዳርጎን ቆይቷል ብለዋል።

የባህር በር የማግኘት ጥያቄው ፍትሐዊ ብቻም ሳይሆን የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ባስጠበቀ ሁኔታ በጋራ የማደግ እሳቤን ያነገበ መሆኑን አስረድተዋል።

በመንግስት እየተካሄደ ያለው ሰላማዊ የባህር በር ጥያቄ የሚደገፍ መሆኑን ጠቁመው ለተግባራዊነቱ በጥናትና ምርምር በማስደገፍ የማሳወቅና የማስገንዝብ ስራ በመስራት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።


 

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሒሳብ መምህር የሆኑት አቶ ማቲዮስ ጌታቸው በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት የውስጥና የወጪ ንግድን በማሳለጥ ህዝቦቿን ከድህነት ለማውጣት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

የባህር በር የማግኘት ጥያቄው ከግል ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍላጎት የመነጨ ሳይሆን በጋራ የመልማት ግብን ይዞ የቀረበ በመሆኑ ተገቢ ምላሽን ይፈልጋል ብለዋል።

የባህር በር ጥያቄው ስኬታማ እንዲሆን በጥናትና ምርምር በተደገፈ አግባብ ጆርናሎችን በማሳተም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቅ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ነው ያሉት።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም