ቀጥታ፡

በዞኑ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውን ለማጉላት የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል

ወላይታ ሶዶ፤ ግንቦት 5/2018 (ኢዜአ)፡-የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውን ለማጉላት የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን  የወላይታ ዞን አስተዳደር ገለጸ።

በዞኑ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችን በአንድ የተቀናጀ መዋቅር (Master Plan) በመምራት የአዋጭነት ጥናት እና የሀብት ምዝገባ ማካሄድ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ ማሟላት፣ የማኅበረሰብ ተሳትፎ እና የሰው ኃይል ልማት፣ የሕግ ማዕቀፍ እና የፋይናንስ ሥርዓት ማዘጋጀትና በዘላቂነት በማስተዋወቅ  የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማጉላት እየተሰራ ነው።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ እንደገለጹት፣ ዞኑ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችን በማልማትና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውን በማጉላት  የማህበረሰቡን  ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው።

ለዚህም በእያንዳንዱ የከተማና የወረዳ መዋቅር አንድ የመስህብ ስፍራን በማልማት የዘርፉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ  እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግም የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አቅም መገንባትና የቱሪስት መዳረሻዎችን ማልማትና ማስተዋወቅ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

የዞኑ ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ፀጋ ፋንታ በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ ባሉ መዋቅሮች በእያንዳንዳቸው አንድ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራ ለማልማት በተያዘው ዕቅድ መሰረት ወደተግባር ተገብቶ እየተሰራ ነው።

ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በዞኑ  ለቱሪዝም ልማት በተሰጠው  ትኩረት  ከ100 በላይ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ እና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻዎች መለየታቸውን ጠቅሰዋል።

እነዚህን የቱሪዝም ሀብቶች በማልማት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም በየመዋቅሩ አንድ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራ የማልማት ዕቅድ  ተይዞ ወደ ተግባር  መግባቱን አንስተዋል።

ይህም  ከዚህ ቀደም ለዘርፉ  የተነፈገውን  ትኩረት በመቀየር  የሀብት ምንጭነት  ለማሳደግ ማገዙን ጠቁመዋል።

በዚህም በዞኑ የጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ  በመምጣቱ  በበጀት ዓመቱ  ዘጠኝ ወራት  68 ሺህ 454 ጎብኚዎች አካባቢውን በመጎብኘት  ከ493 ሺህ ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

በዞኑ የአበላ አባያ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ ዋኬ በበኩላቸው በወረዳው ካሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል የጡባ ኢኮ ቱሪዝም ሳይት አንዱ ነው።


 

ከዞኑ አስተዳደር ጋር በመተባበር ስፍራውን ለቱሪስቶች ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ የልማት ሥራዎች  እንደተጀመሩ ገልጸው፣ መዳረሻውን በማልማት ሥራ ባለሀብቶችም ከ600 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ማዋጣታቸውን ተናግረዋል።

በአባላ አባያ ወረዳ ፍልውሃዎችና በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዳሉት የጠቀሱት አቶ ማቴዎስ፣ አልሚ ባለሀብቶችም በወረዳው መዋዕለንዋያቸውን በማፍሰስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጠይቀዋል። 


 

የዲምቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አሻግሬ ዮሐንስ በበኩላቸው ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በከተማው ለሚገኘው ፍልውሃ የመዳረሻ መንገድ፣ የወጣቶች መዝናኛ እና የመዋኛ ገንዳ በማሟላት ለቱሪስቶች ምቹ  የማድረግ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

መዳረሻውን ይበልጥ ሳቢና ምቹ በማድረግ የጎብኚዎችን ቁጥር ለመጨመርና ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግም ከዞኑ ጋር በመተባበር የማስፋፊያ ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም