የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ ለማሳለጥ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በምርምር የተደገፉ የፖሊሲ ሀሳቦችን ማቅረቡን ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ ለማሳለጥ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በምርምር የተደገፉ የፖሊሲ ሀሳቦችን ማቅረቡን ያጠናክራል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ ለማሳለጥ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በምርምር የተደገፉ የፖሊሲ ሀሳቦችን ማቅረቡን ያጠናክራል ሲሉ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፈቃዱ ፀጋ ገለጹ፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ "መረጃ ለልህቀት፣ የፖሊሲ ሚና ለበለፀገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ የመጀመሪያው የፖሊሲ ቀን መድረክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና ሚኒስትሮች በተገኙበት ተካሂዷል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈቃዱ ፀጋ፥ ኢንስቲትዩቱ ሳይንሳዊ ስነ-ዘዴን በመከተልና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ጥናት በማካሄድ፣ የተለያዩ ፖሊሲዎች እንዲወጡ፣ እንዲስተካከሉ ወይም እንዲሻሻሉ የውሳኔ ሃሳቦችን ለመንግስት እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ስያሜዎች ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፥ በ2011 ዓ.ም የቀድሞውን የኢትዮጵያ የልማት ምርምር ኢንስቲትዩት (EDRI) እና የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከልን በማዋሃድ እንደ አዲስ መዋቀሩን ገልጸዋል።
ይህ አደረጃጀት ሀገራዊ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀምና የምርምር ትብብርን ለማጠናከር ማስቻሉን ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ሀገሪቱ በምታደርገው መዋቅራዊ ሽግግር ነባራዊ ሁኔታዎችንና ህብረተሰባዊ እሴቶችን ያገናዘቡ መፍትሄዎችን በማፍለቅ ረገድ የላቀ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት ከሀገራዊ የልማት አጀንዳዎች አንፃር በ52 የትኩረት የምርምር መስኮች ላይ እየሰራ ይገኛል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በ6 ዋና ዋና የምርምር ማዕከላትና በ14 የፖሊሲ ምርምር ክፍሎች ተዋቅሯል ብለዋል።
ባለፉት ስምንት ዓመታት ብቻ ከ320 በላይ የምርምር ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውንና ከ567 በላይ የምርምር ሪፖርቶች ታትመው ለፖሊሲ ግብዓትነት መብቃታቸውንም አመልክተዋል።
በ2020 የግሎባል ጎቱ ቲንክ ታንክ ኢንዴክስ ሪፖርት መሰረት፣ ኢንስቲትዩቱ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት 8ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን እንደ ትልቅ ስኬት ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ከመንግስት፣ ከግል ዘርፍና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የእውቀት ሽግግርና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ እንደ ሀሳብ መፍለቂያ ተቋምነቱ፣ የፖሊሲዎችን ውጤታማነት የመገምገም፣ የተፅዕኖ ምዘና የማካሄድና አዳዲስ የፖሊሲ አማራጮችን ለፖሊሲ አውጭዎች የማቅረብ ኃላፊነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።