ቀጥታ፡

ለኢንቨስትመንት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ መሰጠቱ ባለሀብቶች ወጪና ተኪ ምርቶች ላይ በትኩረት እንዲሰሩ አድርጓል

ደሴ ፤ ግንቦት 5/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት ለኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠቱ ለወጪ ንግድ የሚቀርቡና ተኪ ምርቶች ላይ በትኩረት እንዲሰሩ ማድረጉን በኮምቦልቻ ከተማ የሚገኙ ባለሃብቶች ገለጹ።

ከባለሀብቶች መካከል የ"ራስ ጉባ" ዱቄትና ብስኩት ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል አበራ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ መንግስት ለግል ባለሃብቱ የሰጠው ትኩረት የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ መልስ እንዲያገኙ እያደረገ ነው።

የተሰጠው ፈጣን ምላሽ ለተኪና ለወጪ ንግድ የሚሆኑ ምርቶችን ማምረት እንድንችል ያደረገ ነው ያሉ ሲሆን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም የዘርፉን ችግሮች በመፍታት ባለሃብቱ እንዲነቃቃ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት በውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ብስኩትን በሀገር ውስጥ ምርት ከመተካት ባለፈ ለውጪ ንግድ ለማቅረብ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።


 

የ "ዋሊያ" ቆርኬ ፋብሪካ ተወካይ አቶ ታምሩ አለባቸው በበኩላቸው፣ መንግስት ለኢንቨስትመንት መስኩ የሰጠው ትኩረት ፈጥነን ወደ ምርት እንድንገባና ተጠቃሚ ለመሆን እንድንችል አድርጎናል ብለዋል።

በቀን ከ 6 ሺህ በላይ የለስላሳ ጠርሙስ ክዳን  ቆርኪዎችን  በማምረት ከውጭ የሚመጣውን  ምርት ለመተካት መቻሉንም ነው የተናገሩት።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሀመድአሚን የሱፍ በበኩላቸው፣ ባለፉት ዓመታት ለኢንቨስትመንት ዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል፡፡


 

በተለይ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መካሔዱ በአካባቢው ያሉ ኢንዱስትሪዎች የነበራቸውን 47 በመቶ  የማምረት አቅም ከ60 በመቶ በላይ ማድረስ ማስቻሉንም ገልጸዋል።

ባለፉት 9 ወራትም ኢንዱስትሪዎቹ  ወደ ውጭ ከላኳቸው ምርቶች ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘት ከመቻሉም በላይ ከ70 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚሆን ተኪ ምርት እንዳመረቱም  ተናግረዋል።

በቀጣይም በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማስተካከል ተኪና ወጪ ምርት በማምረት ስራ ላይ በማተኮር እንዲሰራም ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ነው ያሉት።

"ኢትዮጵያ ታምርት፣ እኛም እንሸምት" በሚል መሪ ሀሳብ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት የምክክር መድረክ ማካሄዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም