ቀጥታ፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን ለመኸር እርሻው ከ660 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ነው

ደብረ ማርቆስ፤ ግንቦት 5/2018(ኢዜአ)፦በምስራቅ ጎጃም ዞን ለመኸር እርሻው የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ታቅዶ እየተከናወነ ባለው ተግባር እስካሁን ከ660 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለተጠቃሚው ማቅረብ መቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ምክትል ሃላፊ አቶ ጥላሁን ንጋቱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በመጪው የመኸር ምርት ዘመን የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ የቤተሰብን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ምርትን ለገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።


 

በዞኑ ለዘንድሮው የመኸር እርሻ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማስገባት ታቅዶ እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ ከ660 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነውን ወደ ዞኑ በማስገባት ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ወደ ዞኑ ከገባው ማዳበሪያ ውስጥም እስካሁን ከ300 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነውን ቀድመው ለሚዘሩ አርሶ አደሮች የማሰራጨት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

ዞኑ ትርፍ አምራች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለክልሉም ሆነ ለሀገር ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ የታቀደውን ማዳበሪያ ሙሉ በሙሉ ለማስገባት እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ይህም በመኸር ወቅት ለማምረት የታቀደውን ከ26 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።

የገባውን ማዳበሪያም ቀድመው ለሚዘሩና በክረምት ዝናብ ምክንያት የትራንስፖርት ችግር ለሚያጋጥማቸው አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት የማሰራጨት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።


 

ከተጠቃሚዎች መካከል በሸበል በረንታ የድውሃ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ሆድሞኝ ዳምጤ እንዳሉት፤ ለበቆሎ  ዘር የሚውል አንድ  ኩንታል ተኩል ማዳበሪያ ቀድመው መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

የአፈር ማዳበሪያ ቀድሞ መቅረቡ በወቅቱ በመዝራት የሚጠብቁትን ምርት ለማግኘት እንደሚያስችላቸው  ተናግረዋል።

በደብረ ኤሊያስ  ወረዳ የጓይ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገናነው አዘነ በበኩላቸው፤ ለምርት ዘመኑ ለሚዘሩት  የስንዴና የበቆሎ ሰብል አራት ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መውሰድ ችያለሁ ብለዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም