ቀጥታ፡

የሲዳማ ክልል መምህራን ማህበር የሕብረተሰቡ የምርጫ ተሳትፎ እንዲጎለብት ሃላፊነቱን እየተወጣ ነው

ሀዋሳ፤ ግንቦት 5/2018(ኢዜአ)፦ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት ማህበረሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ የሚያስችል የግንዛቤ ማጎልበቻ ትምህርት በመስጠት ሙያዊና ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን የሲዳማ ክልል መምህራን ማህበር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመራጮች ትምህርት ላይ ለሚሠማሩ 169 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዕውቅና መስጠቱ ይታወቃል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ኢያሱ ፍቅሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ማህበሩ በታዛቢነትና በመራጮች ትምህርት ላይ እንዲሳተፍ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ተሰጥቶታል።

በዚህም ህብረተሰቡ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት እንዲሳተፍ በማስተማርና ግንዛቤውን በማሳደግ ግዴታውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

የምርጫውን ሂደት በታዛቢነት የሚከታተሉ መምህራንንም ከአባላቱ ውስጥ መልምሎ ማቅረቡን ጠቅሰዋል፡፡

ለምርጫው ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊነት ዜጎች የላቀ ተሳትፎ እንዲያደርጉም በማህበሩ አባላት በኩል የማስገንዘብና የማስተማር ሥራ እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ለዚህም ከወረዳ እስከ ክልል በየደረጃው ላሉ የማህበሩ አመራሮችና አባላት ሥልጠና ተሰጥቶ ወደሥራ መገባቱን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም