ቀጥታ፡

ያገኘነውን የመጀመሪያ ዕድል ሳናባክን ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ለመጠቀም ካርድ ወስደናል - የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

ወላይታ ሶዶ ፤ ግንቦት 5/2018(ኢዜአ)፦ለመምረጥ ብቁ የሆኑበትን የመጀመሪያ ዕድል ሳያባክኑ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም ካርድ መውሰዳቸውን የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እንዲሳተፉ በየተቋማቱ የምርጫ ጣቢያዎችን በማቋቋም ካርድ እንዲወስዱ ማድረጉ ይታወቃል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፤ በዘንድሮ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የመሳተፍ ዕድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። 

ተማሪ ኪሩቤል ተፈሪ እንደገለጸው፤ተማሪዎች በምርጫው እንዲሳተፉ በተፈጠረላቸው ዕድል መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ ለመሳተፍ ካርድ ወስዷል።

በወሰድኩት ካርድ የመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብቴን ተጠቅሜ ለነገ ሀገር ግንባታና ቀጣይነት የተሻለ አማራጭ ፖሊሲ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ብሏል።

ተማሪ ተስፋነሽ ጮራሞ በምርጫው ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሳተፍ ካርድ በመውሰዷ ዕድለኛ መሆኗን ተናግራለች።

በድምጿም የተሻለ አማራጭ ሀሳብና የትምህርት ፖሊሲ ያለው እንዲሁም ለሴቶች ተጠቃሚነት የሚሰራ ፓርቲን ለመምረጥ ማቀዷን ገልፃለች።

መምረጥና መመረጥ በህገ መንግስት የተጎናጸፍነው ዲሞክራሲያዊ መብታችን ነው ያለችው ተማሪ ተስፋነሽ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን ብላለች።

ቢንያም ደምሌ እና ፍሬው ወዳሎ የተባሉ ተማሪዎች በበኩላቸው፤ በመጀመሪያው የምርጫ ተሳትፎ በወሰዱት ካርድ የሀገርን ሰላም በማፅናት ጠንካራ የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ የሚያደርግ ፓርቲን እንደሚመርጡ ገልጸዋል።

እንዲሁም ለወጣቱ ትውልድ የስራ አማራጭ የሚፈጥር ፓርቲ ለመምረጥ ዕለቱን በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለማካሄድ መርሃ ግብር አውጥቶ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም