ቀጥታ፡

የመስኖ ልማት የአርሶ አደሩን የሥራ ባህል በመቀየር በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ ለማምረት አስችሏል

አዳማ ፤ ግንቦት 5/2018(ኢዜአ)፦የመስኖ ልማት የዝናብ ወቅትን ብቻ ጠብቆ በማረስ የሚከሰተውን የምርት እጥረት ከመቅረፉም ባለፈ፣ የአርሶአደሩን የሥራ ባህል በመቀየር በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ ማምረት እንዲችል ማገዙን በምስራቅ ሸዋ ዞን መስኖና አርብቶ አደር ልማት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። 

ባለፉት የለውጥ ዓመታት 301 ሺህ ሄክታር መሬትን በመስኖ ማልማት የሚያስችሉ ከ 20 ሺህ በላይ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች መሰራጨታቸውም ተገልጿል።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዑመርሰን ሌንጫሞ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ በሚስተዋለው የዝናብ እጥረት የሚከሰተውን የምርት መቀነስ ለማካካስ፣ የገፀ-ምድርና የከርስ-ምድር የውሃ ሀብቶችን በመጠቀም ለመስኖ ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል። 

ይህንን ተግባር ይበልጥ ለማጠናከርም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 1 ሺህ 510 የውሃ መሳቢያ ጄኔሬተሮች ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ ተደራሽ ተደርገዋል።

ለአርሶ አደሩ ከቀረቡት ጄኔሬተሮች መካከልም የአካባቢ ብክለትን የሚቀንሱና ወጪ ቆጣቢ የሆኑ 18 በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ሞተሮች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

ከኦሮሚያ ክልል መስኖና አርብቶ አደር ልማት ቢሮና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር 27 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ተቆፍረው ለአገልግሎት የበቁ ሲሆን፣ በዚህም 22 ሺህ ሄክታር ተጨማሪ መሬት ወደ መስኖ ልማት ማስገባት ተችሏል ብለዋል።

ለአብነትም ፊና ብስኬ፣ ቦፋ ወለንጪቲ፣ ቦሰት ፈንታሌ እና ላፌሳ የተባሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች በአሁኑ ወቅት በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። 

በተጨማሪም የቦራና የቦሰት ፋንታሌ ሁለተኛ ምዕራፍ የማስፋፊያ ግንባታዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የመስኖ ልማቱ አርሶ አደሩ የዝናብ ወቅትን ብቻ ጠብቆ በማረስ የሚከሰተውን የምርት እጥረት ከመቅረፉም ባለፈ፣ የሥራ ባህልን በመቀየር በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ ማምረት እንዲችል አግዟል ነው ያሉት። 

ይህም ቀደም ሲል በአካባቢው በሴፍትኔት መርሃ-ግብር ይታቀፉ የነበሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ከተረጂነት አላቆ ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ በማድረግ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑ ተጠቁሟል።

በዞኑ እየተካሄደ ያለው የመስኖ ልማት የአመራረት ባህልን በመቀየር ረገድም ከፍተኛ ሚና ያለው ሲሆን፣ አርሶ አደሮች በበጋ መስኖ ስንዴ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ብርቱካን፣ ሎሚ፣ ቲማቲምና ሌሎች ገበያ ተኮር አትክልትና ፍራፍሬዎች ልማት ላይ በስፋት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም