ኢትዮጵያ በ24ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመጀመሪያ ሜዳሊያዋን አገኘች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በ24ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመጀመሪያ ሜዳሊያዋን አገኘች
አዲሰ አበባ፤ ግንቦት 5/2018 (ኢዜአ)፦ 24ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትናንት በጋና አክራ ተጀምሯል።
በሻምፒዮናው መክፈቻ ቀን በተደረገው የ5000 ሴቶች የፍጻሜ ውድድር አትሌት ዘይን አየልኝ ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች።
ይህም ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ላይ ያገኘችው የመጀመሪያ ሜዳሊያ ሆኖ መመዝገቡን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በ400 ሜትር ሴቶች ማጣሪያ አትሌት አጃይባ አሊዬ በምድብ ሁለት አንደኛ በመውጣት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋለች።
በወንዶች ርዝመት ዝላይ ማጣሪያ አትሌት ቡሊ መላኩ ለፍፃሜ አልፏል።
በ100 ሜትር ሴቶች ማጣሪያ የተሳተፉት አትሌት ተሊሌ ታከለ እና አትሌት ሰላማዊት ኮከብ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ አልቻሉም።
በ400 ሜትር መሰናክል ወንዶች ማጣሪያ የተወዳደረው አትሌት ጌታሁን ታደሰ አምስተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ሳይችል መቅረቱን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።
በጋና ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እየተካሄደ በሚገኘው ሻምፒዮና ላይ ከ54 ሀገራት የተወጣጡ አትሌቶች ተሳታፊ ሆነዋል።
ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ 31 ሴቶች እና 32 ወንዶች በድምሩ 63 አትሌቶችን አሳትፋለች።
ሻምፒዮናው እስከ ግንቦት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።