የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከግብጽ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከግብጽ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2018 (ኢዜአ)፦ በሞሮኮ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ይጀመራል።
በውድድሩ ላይ 16 ሀገራት ተሳታፊ ሆነዋል።
ኢትዮጵያም በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ሞሮኮ፣ቱኒዚያ እና ግብጽ ጋር ተደልድላ ጨዋታዋን ታደርጋለች።
ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ከግብጽ ጋር በመሐመድ ስድስተኛ እግር ኳስ ኮምፕሌክስ ያደርጋል።
በአሜሪካው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለውድድሩ በአዲስ አበባ የነበረውን ዝግጅት አጠናቆ ሞሮኮ በመግባት ባለፉት ቀናት ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
ብሔራዊ ቡድን ከዛሬው ጨዋታ አስቀድሞ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት ማከናወኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር ከጨዋታው በፊት በሰጡት አስተያየት ግባችን ለዓለም ዋንጫ ማለፍ ነው፤ ቡድኑም ለዚህ ዝግጁ ነው ብለዋል።
ከግብጽ ጋር ለሚደረገው ጨዋታም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።
ብሔራዊ ቡድኑ በሕዳር ወር 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሶስተኛ መውጣቱን ተከትሎ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ የሚታወስ ነው።
በዚሁ ምድብ ምሽት አራት ሰዓት ላይ አዘጋጇ ሞሮኮ ከቱኒዚያ ጋር ጨዋታዋን ታደርጋለች።
ተጫዋቾቹ እና የቡድን አባላቱ ኢትዮጵያን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የማሳለፍ ታሪካዊ አደራ ተቀብለው ወደ ሞሮኮ አምርተዋል።
በአፍሪካ ዋንጫው በምድብ ሁለት ኮትዲቯር፣ ካሜሮን፣ ዩጋንዳ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተደልድለዋል።
ማሊ፣ አንጎላ፣ ታንዛንያ እና ሞዛምቢክ በምድብ ሶስት የሚገኙ ሀገራት ናቸው።
ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አልጄሪያ እና ጋና የሚገኙበት ምድብ አራት ጠንካራው ምድብ ነው።
16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ እስከ ግንቦት 25 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
በአፍሪካ ዋንጫው ከሚሳተፉ 16 ሀገራት መካከል የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ 10 ሀገራት በጥቅምት እና ህዳር ወር 2019 ዓ.ም በኳታር ለሚካሄደው 20ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ያልፋሉ።