ቀጥታ፡

የምርጫ ሂደቱ በሰለጠነ የክርክር አግባብ በሃሳብ የበላይነት ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ መሰረት እያኖረ ነው 

አሶሳ፤ ግንቦት 5/2018(ኢዜአ)፦ የዘንድሮው የምርጫ ሂደት በሰለጠነ የክርክር አግባብ በሃሳብ የበላይነት ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ መሰረት እያኖረ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት ሰብሳቢ አብዱሰላም ሸንገል ተናገሩ።

የክርክር ሂደቱና የምረጡኝ ቅስቀሳውም ዜጎች ፖሊሲና የሃሳብ የበላይነት ላይ ተመስርተው መምረጥ እንዲችሉ እድል የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ከመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጋር በመተባበር የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ሚዲያዎች በተሰጣቸው ነፃ የአየር ሰዓት የፓርቲያቸውን ማኒፌስቶ እና የፖሊሲ አማራጭ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች በተሰጣቸው የአየር ሰዓት የፓርቲያቸውን የፖሊሲ አማራጮች እያስተዋወቁና የምረጡኝ መልእክቶቻቸውን እያስተላለፉ ይገኛሉ።

የቤኒሻንጉል ህዝብ ነፃነት ንቅናቄ ፓርቲ ሊቀመንበር እና የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት ሰብሳቢ አብዱሰላም ሸንገል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የዘንድሮው የምርጫ ሂደት በብዙ መልኩ ጥሩ እንቅስቃሴ የታየበት ነው።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በክርክር መድረኮች በሃሳብ የበላይነት ለምርጫው የሚያደርጉትን ፉክክር አጠናክረው ቀጥለዋል ብለዋል።

በተሰጣቸው እድልና በተለያዩ አማራጮች ወደ ህዝቡ ተደራሽ በመሆን ፖሊሲና ስትራቴጂያቸውን እያስተዋወቁ መሆኑንም ተናግረዋል።

የዘንድሮው የምርጫ ሂደት በሰለጠነ የክርክር አግባብ በሃሳብ የበላይነት ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ መሰረት እያኖረ መሆኑን  ገልጸዋል።

በክርክር ሂደቶችና የምረጡኝ ቅስቀሳ ዜጎች የፓርቲዎችን ፖሊሲና የሃሳብ የበላይነት በቅጡ በመገንዘብ መምረጥ የሚችሉበት እድል እየተፈጠረ ስለመሆኑም አንስተዋል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ መስጫ እለት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑን በቦርዱ ይፋ የተደረገው መርሃ ግብር ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም