ቀጥታ፡

የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የከፍተኛ ደረጃ ውይይት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2018(ኢዜአ)፦ 10ኛው የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የከፍተኛ ደረጃ ውይይት በሕብረቱ ዋና መቀመጫ ዛሬ በአዲስ አበባ ይደረጋል።

በውይይቱ ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንደሚገኙ ይጠበቃል።

ውይይቱ በሁለቱ ወገኖች መካከል በአፍሪካ ልማት እና በዓለም አቀፍ አስተዳደር ዙሪያ ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማጠናከርን ያለመ ነው።

በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ያለውን ቅንጅት፣ የጋራ ተጠያቂነት እና ትብብርን በልማት፣ በአስተዳደር፣ በሰብአዊ ድጋፍ እና በሰላም ግንባታ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ያላቸውን ትስስር ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ይካሄዳል።

በዚህ የከፍተኛ ደረጃ ውይይት ላይ በርካታ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች የሚዳሰሱ ሲሆን፣ በተለይም የአጀንዳ 2063 እና የሁለተኛው የአስር ዓመት ምዕራፍ የትግበራ ዕቅድ አፈፃፀምን ማፋጠን እንዲሁም አፍሪካን በዓለም አቀፍ ፖሊሲ እና አስተዳደር ውስጥ ያላትን ማዕከላዊ ሚና መጠበቅ በሚሉ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ያደርጋል።

በተጨማሪም "ከጥገኝነት ወደ ሉዓላዊነት" የተሸጋገረ የልማት ፋይናንስ፣ የ2026 የአፍሪካ ሕብረት የዓመቱ መሪ ቃል የሆነው ዘላቂ የውሃ አቅርቦት እና የንጽህና አጠባበቅ፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት ሪፎርም እና አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ያላትን ውክልና የተመለከቱ ጉዳዮች ውይይት ይደረግባቸዋል።

መድረኩ ለአህጉራዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎችን ማምጣት፣ የአገር ውስጥ ሀብት ማሰባሰብን ማሳደግ፣ የወጣቶች እና የሴቶች ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዲሁም በአህጉራዊ እና በዓለም አቀፍ የልማት የቅድሚያ ትኩረቶች መካከል ያለውን ትስስር ማጠናከር ወሳኝ መሆኑ አጽንኦት የሚሰጥበት እንደሆነ ተመላክቷል።

ከውይይቱ ከሚጠበቁ ውጤቶች መካከል የተሻለ ስትራቴጂካዊ ቅንጅት፣ ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ለውጥ፣ በአፍሪካ ህብረት የዓመቱ መሪ ቃል ዙሪያ ጠንካራ ቅንጅት መፍጠር እና በተባበሩት መንግሥታት ሥርዓት ውስጥ ፍትሐዊ የአፍሪካ ውክልና እንዲኖር የቀረቡ ጥሪዎችን ማጠናከር እንደሚገኙበት ህብረቱ ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የውይይቱን ውጤቶች አስመልክቶ የጋራ መግለጫ ይሰጣሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም