ወጣቶች የአረጋውያንን የካበተ የሕይወት ልምድ በመቅሰም ለኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት መጠቀም ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች የአረጋውያንን የካበተ የሕይወት ልምድ በመቅሰም ለኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት መጠቀም ይጠበቅባቸዋል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 4/2018(ኢዜአ)፦ ወጣቶች የአረጋውያንን የካበተ የሕይወት ልምድ በመቅሰም ለኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት መጠቀም እንዳለባቸው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ገለፁ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ'ሄልፕ ኤጅ ኢትዮጵያ' ጋር በመተባበር የአረጋውያንን ውጤታማ የሕይወት ተሞክሮ ለተተኪ ትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል የውይይት መድረክ አካሂዷል።
መድረኩም አረጋውያን በህይወት ዘመናቸው ያካበቱትን ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ተሞክሮና ሥነ-ልቦና ጥንካሬ ለተተኪ ትውልድ ለማስተላለፍ ያለመ ነው።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በዚሁ ወቅት፤ አረጋውያን ለሀገር ልማትና ዕድገት አቅም የሚሆን የካበተ ልምድና ተሞክሮ አላቸው ብለዋል።
በዚህም የአረጋውያንን ሰብዓዊ ክብር በመጠበቅ ዕውቀት፣ ልምድና የሥነ-ልቦና ጥንካሬ ተሞክሯቸውን ለተተኪ ትውልድ እንዲያስተላልፉ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አረጋውያንም የሕይወት ልምድና ተሞክሯቸውን ለተተኪ ትውልድ በማስተላለፍ ለሀገር ልማትና ዕድገት፣ ለህዝብ አብሮነትና አንድነት መጎልበት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።
አረጋውያን ለሀገር ልማት፣ አንድነትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በማስቀጠል መብትና ጥቅማቸው እንዲከበር ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ወጣቱ ትውልድም ከአረጋውያን ጥበብን በመቅሰም ለራሱም ሆነ ለማህበረሰብ ሁለንተናዊ ለውጥ ገንቢ ሚና መወጣት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ክፍሉ፤ የወጣቶችን ስብዕና በመገንባት የትውልድ ቅብብሎሽ ድልድይነታችንን በሚገባ መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ወጣቶችም የአረጋውያንን በህይወት ልምድ የካበተ ዕውቀትና ክህሎት በመጋራት ለሀገር ግንባታና ዕድገት መጠቀም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የራስወርቅ አድማሴ በበኩላቸው፤ የአሁኑ ትውልድ የአረጋውያንን የካበተ ልምድ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በማሰናሰል ለሀገር ልማት መጠቀም አለበት ብለዋል።
በመድረኩ ከተሳተፉ ወጣቶች መካከል ወጣት ዳዊት ተክለፃዲቅ፤ የአረጋውያንን ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ በተሻለ የትውልድ ቅብብሎት ጠንካራ ሀገር ግንባታ እንጠቀምበታል ብሏል፡፡