የሀገርን ጥቅም በሚጎዱ ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ላይ የተጠናከረ ሥራ ተሰርቷል - ኢዜአ አማርኛ
የሀገርን ጥቅም በሚጎዱ ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ላይ የተጠናከረ ሥራ ተሰርቷል
አዲስ አበባ፤ግንቦት 4/2018(ኢዜአ)፦የሀገርን ጥቅም በሚጎዱ ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ላይ የተጠናከረ ሥራ መሰራቱን የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና ተቋማዊ ሪፎርም የገቢ አሰባሰብ አቅምን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃፀም በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥቷል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ (ዶ/ር) በመግለጫቸው፤ የኢትዮጵያን ፋይናንስ የማመንጨት አቅም ለማሳደግ በበጀት ዓመቱ 725 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ አስር ወራትም 598 ነጥብ 91 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ በተያዘው ዕቅድ መሠረት፤ 600 ነጥብ 23 ቢሊዮን ብር በላይ ጥቅል ገቢ በመሰብሰብ ከዕቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን አስታውቀዋል።
የዘንድሮው አፈፃጸም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው ጋር ሲነፃፀር የ75 ነጥብ 29 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል።
ጠንካራ የድጋፍና ክትትል፣ ፍትሕዊና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት፣ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከርና በኮንትሮባንድን መከላከል የተሰራው ውጤታማ ሥራ ለዕቅዱ ስኬት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
በተጨማሪም በተከታታይ የተወሰዱ ተቋማዊ የሪፎርም፣ የአመራርና ሙያተኛ አቅም ግንባታ ተግባራትን በየሩብ ዓመቱ በመገምገም የገቢ አሰባሰብ ውጤታማነትን ማሳደግ እንደተቻለ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለዘመናት የታሰረውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በማፍታታትና ተቋማዊ የገቢ አሰባሰብ አቅምን በማጎልበት ውጤታማነትን እንዳሳደገ ጠቅሰዋል።
በጉምሩክ ኮሚሽን የሚሰበሰብ ገቢም የመንግሥትን የፋይናንስ አቅም በማጎልበት የመሠረተ ልማት ግንባታን በማሳለጥ ለኢንቨስትመንት ፍሰት አቅም እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
የተወሰዱ ተቋማዊ የሪፎርም እርምጃዎችም የሕግ- የቴክኖሎጂና የአደረጃጀት ውጤታማነትን በማሳደግ የገቢ አሰባሰብ አቅምን እያጎለበተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የመንግስት ተከታታይ ሁሉን አቀፍ ሪፎርም እርምጃም ዘመናዊ አሰራርን መዘርጋት በገቢ አሰባሰብ ላይ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በበጀት ዓመቱ አስር ወራት ውስጥ በድንገተኛ ፍተሻ ተለይተው ከተፈተሹ ሰነዶች ወደ ገቢ የሚቀየር ሁለት ነጥብ 864 ቢሊዮን ብር መገኘቱን አስረድተዋል።
ይህም የሀገርን ጥቅም በሚጎዱ ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ላይ የተጠናከረ ሥራ መሰራቱን እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ አስር ወራት በሕገ-ወጥ ንግድ፣ ማጭበርበርና ኮንትሮባንድ ህብረተሰቡን በማስተባበር፣ የውስጥ አቅምን በማጠናከርና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ከ279 ነጥብ 855 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን እንደተቻለ ገልጸዋል።
ከገቢ ኮንትሮባንድ ብቻ ከ21 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸው፤ ማዕድናት፣ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ያለተፈቀደላቸው መድሃኒቶች፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ይገኙበታል ብለዋል፡፡