ቀጥታ፡

በክልሉ ከ306 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጥቷል

ኮምቦልቻ ፤ ግንቦት 4/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ306 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰጠቱን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር "ኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት" በሚል መሪ ሃሳብ የኢንቨስትመንት ንቅናቄ መድረክ ዛሬ አካሂዷል።


 

የቢሮ ኃላፊው አቶ እንድሪስ አብዱ እንደገለፁት፣ ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር በመፍታት፣ ተቋማዊ ቅንጅትና ትስስር መፍጠርን ጨምሮ ዘርፉን በማሳደግ ውጤት እንዲመዘገብ የሚያደርግ ነው።

ባለፉት ዘጠኝ ወራትም 306 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ሁለት ሺህ 925 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መስጠት መቻሉን ገልጸዋል።


 

ክልሉ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ባደረገው ድጋፍ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 137 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት የገቡ ሲሆን ለ64 ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻላቸውን ተናግረዋል።

ችግሮችን በቅንጅት ለመፍታት በተደረገው ጥረትም የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 62 ነጥብ አራት  በመቶ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስትም 567 ሚሊዮን ብር በመመደብ የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራትና የሌሎች የመሰረተ ልማት ተግባራትን በማከናወን የሚነሱ ጥያቄዎች መመለስ መቻሉን አስረድተዋል።

ክልሉ በተለይም ኮምቦልቻ ከተማ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተመራጭ እየሆነች መምጣቷ ለዘርፉ መነቃቃት አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሁሴን ሙሄ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዘርፉን እያነቃቃ መሆኑን ነው የተናገሩት።


 

ባለፉት ዘጠኝ ወራትም 28 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 84 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰጠቱንና 6 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን በማሳያነት አንስተዋል።

በመድረኩ የክልልና የከተማ አመራሮች፣ ባለድርሻ አካላትና ባለሃብቶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም