ዩኒቨርሲቲው በምርምር ያወጣቸው የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች ከእንስሳት ሀብት የሚገኘውን ምርታማነት ያሳድጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው በምርምር ያወጣቸው የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች ከእንስሳት ሀብት የሚገኘውን ምርታማነት ያሳድጋሉ
አሶሳ፤ ግንቦት 4/2018(ኢዜአ)፦ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ያወጣቸው የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች በክልሉ ያለውን የእንስሳት ምርታማነት ለማሳደግ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ማዕከል በቆላማ አካባቢዎች የተሻለ ምርት የሚሰጡና ከአየር ንብረቱ ጋር የሚስማሙ የተሻሻሉ የፍየል ዝርያዎችን ለኡራ ወረዳ አርሶ አደሮች አሰራጭቷል።
ይህ የዝርያ ማሻሻያ ስራ በአካባቢው ያለውን የእንስሳት ሀብት ምርታማነት ለማሳደግና የአርሶ አደሩን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ብርሃኑ ኢትቻ በወቅቱ እንዳሉት፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ግብርናውን በሁሉም ዘርፍ የማዘመን ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
በተለይም የእንስሳት ዘርፉን ለማሳደግ እየተከናወኑ የሚገኙ አዳዲስ የዝርያ ማሻሻያዎች ከዘርፉ የሚገኘውን ምርታማነት በማሳደግ የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት እያሳደጉ ነው ብለዋል።
ክልሉ ከመደበኛ ግብርና ስራ በተጨማሪ ለእንስሳት እርባታ ምቹ መሆኑን ጠቁመው የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምር ማዕከል ለአርሶአደሩ ያሰራጫቸው የተሻሻሉ የፍየል ዝርያዎች አርሶአደሩ በእንስሳት እርባታ ዘርፍ በስፋት እንዲሰማራ በማድረግ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዑመር ሸሪፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በተሰጠው የተግባር ተኮር የምርምር መስክ ግብርናን በማዘመን ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው ምርምር ማዕከል በዛሬው ዕለት ለአርሶአደሮች ያሰራጫቸው የፍየል ወጠጤዎች ለሶስት ዓመታት ምርምር የተካሄደባቸው እና የአካባቢውን አየር ሁኔታ የተላመዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አርሶአደሮቹ የተረከቡትን ፍየል አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግ ለእርባታ ብቻ መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል።