በክልሉ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ባህር ዳር፤ ግንቦት 4/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
ብልጽግና ፓርቲ "ኢትዮጵያን ወደተምሳሌት ሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ በባህር ዳር ከተማ ለወጣቶች ባዘጋጀው መድረክ የምርጫ ቅስቀሳና ሚኒፌስቶውን አስተዋውቋል።
በቢሮው የወጣቶች ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘለዓለም አረጋ በመድረኩ እንደገለጹት በብልጽግና ፓርቲ መሪነት ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሸጋገር በሁሉም የልማት ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ፣ የበጋ ስንዴ ልማት አብዮት በመፍጠር፣ አረንጓዴ አሻራን በመተግበር፣ የሌማት ትሩፋትን እውን በማድረግና በሌሎች ዘርፎችም ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተጋ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ወጣቱን በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀቱን በማሳደግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ በተሰራው ሥራ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ በግብርናው ዘርፍ የታዩ እመርታዎች በምግብ ራስን ለመቻልና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተያዙ ግቦችን በማሳካት ህዝብን በዘላቂነት ተጠቃሚ ያደረጉ ናቸው ብለዋል።
የተገነቡ ፕሮጀክቶች የክልሉ ወጣቶችንም ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ማረጋገጣቸውን ጠቁመው፣ በቀጣይም ይሄ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲቀጥል ወጣቶች ድምጻቸውን ለሚፈልጉት ፓርቲ በነጻነት ከመስጠት ባለፈ ለጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ተአማኒነት የበኩላቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የወጣቶች ክንፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት ተስፋሁን ተሰማ በበኩሉ ወጣቶች ሀገር ተረካቢ ብቻ ሳይሆኑ ሀገር ሰሪም ናቸው ብሏል።
እስካሁን በልማቱ ያደረጉትን ተሳትፎ በማጠናከር 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የራሳቸውን አሻራ ሊያሳርፉ ይገባል ሲልም ተናግሯል።
"ወጣቱ የሚፈልገውን የፖለቲካ ፓርቲ በመምረጥ የተጀመረውን ልማት ማስቀጠል አለበት" ያሉት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሰብለ ዘውዱ ናቸው።
የተጀመሩ ትላልቅ ሜጋ እና ከባቢያዊ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ወጣቱ ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ራሱን ማዘጋጀት አለበት ሲሉም ተናግረዋል።