ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአትሌት የብርጓል መለሰ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 4/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጀግናዋ የረጅም ርቀት አትሌት የብርጓል መለሰ በመደበኛ ልምምድ ላይ እያለች ዛሬ ጠዋት በደረሰባት ድንገተኛ ህልፈተ ሕይወት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል።
 
አትሌት የብርጓል መለሰ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያን በመወከል ስኬታማ ተሳትፎ ያደረገች ሲሆን፤ በተለይም እ.ኤ.አ በ2015 በኮንጎ ብራዛቪል በተካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በግማሽ ማራቶን የነሐስ ሜዳሊያ በማስገኘት ሀገሯን አስጠርታለች።
 
በተጨማሪም በዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ውድድሮች ደማቅ ታሪክ ያላት አትሌቷ፤ በ2015ቱ የቺካጎ ማራቶን የብር ሜዳሊያ ባለቤት ከመሆኗም ባለፈ የሻንጋይ፣ የፕራግ እና የሁውስተን ማራቶኖች አሸናፊ ነበረች።
 
እንዲሁም የፓሪስ ግማሽ ማራቶንን ለሁለት ጊዜያት፣ የሊዝበን ግማሽ ማራቶንን ደግሞ አንድ ጊዜ በአንደኝነት ማጠናቀቋ ይታወሳል።
 
ጀግናዋ አትሌት የብርጓል መለሰ ህይወቷ ከማለፉ በፊት በካናዳ በሚካሄደው የኦታዋ ማራቶን ለመሳተፍ ዝግጅት ላይ እንደነበረች ተገልጿል።
 
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአትሌቷ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፤ ለቤተሰቦቿ፣ ለወዳጅ ዘመዶቿ፣ ለአድናቂዎቿና ለመላው የስፖርት ቤተሰብ መጽናናትን ተመኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም