ቀጥታ፡

የጤና ተቋማትና የግብዓት አቅርቦት ተደራሽነትን የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 4/2018(ኢዜአ)፦ የጤና ተቋማትና የግብዓት አቅርቦት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው አምስተኛ የስራ ዘመን 20ኛ መደበኛ ስብሰባ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።


 

የምክር ቤቱ አባላት ሚኒስቴሩ በወረርሽኝ አፋጣኝ ምላሽ በተለይም የማርበርግ ቫይረስን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር ያከናወነው ተግባር የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠትና የህክምና ግብዓት ለማሟላት እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች ውጤት የተመዘገበበት መሆኑንም አባላቱ አንስተዋል።

ሚኒስቴሩ የጤና ተቋማት ተደራሽነትና በአንዳንድ አካባቢዎች የተጀመሩ የጤና ተቋማት ግንባታ መጓተት ችግሮችን ለመፍታት ምን እየሰራ እንደሚገኝ ጠይቀዋል።

የመድሃኒት አቅርቦትና የመረጃ ስርጭት፣ የህክምና ግብዓቶች ማከማቻ መጋዘን እንዲሁም የላቦራቶሪ ተደራሽነት ጥያቄዎችም ቀርበዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ በጤናው ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ በስራ ዘመኑ የጤናው ዘርፍ የጀርባ አጥንት የሆኑ አስቻይ አዋጆችን ማፅደቁንና በሚኒስትሮች ምክር ቤትም በርካታ ደንቦች መፅደቃቸውን ገልፀዋል።

ለጤናው ዘርፍ የመሰረተ ልማት፣ ባለሙያና ግብዓቶች ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የጤና አገልግሎት ጥራት፣ ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ ግንባታዎች መከናወናቸውን አንስተው፤ የግል ጤና ተቋማት ቁጥርም ከነበረበት 7ሺህ ወደ 30ሺህ ማደጉን ጠቅሰዋል።

የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤን የማስፋትና ግብዓት የማሟላት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የምክር ቤት አባላቱ ባነሷቸው አካባቢዎች የጤና አገልግሎት ጥራት፣ ፍትሃዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ከ60 ሚሊየን በላይ ዜጎች የጤና አገልግሎት ለማግኘት መመዝገባቸውንና ከ55ሚሊየን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል።

መንግሥት በሆስፒታሎች የነበሩ በርካታ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅና መሰረተ ልማት እንዲሁም ግብዓቶችን ለማሟላት ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ አንስተዋል።

የመድኃኒትና ህክምና ማከማቻ መጋዘኖችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ባሉት 19 ቅርንጫፎችና ከ50 በላይ መጋዘኖች የዲጂታል አሰራርን በመተግበር ስራውን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም