ቀጥታ፡

በዞኑ ከሰብል ልማት ጎን ለጎን ለንብ ማነብ ሥራ ትኩረት ተሰጥቷል

መቱ፤ ግንቦት 4/2018 (ኢዜአ)፡-በኢሉባቦር ዞን የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከሰብል ልማት ጎን ለጎን ለንብ ማነብ ሥራ ትኩረት መሰጠቱን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።  

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አዳሙ ታከለ ለኢዜአ እንዳሉት በዞኑ ተግባራዊ ከተደረጉ የግብርና ልማት ኢኒሼቲቮች መካከል የንብ ማነብ ሥራ አንዱ ነው።


 

ኢኒሼቲቩን ውጤታማ በማድረግ የአርሶ ደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከአረንጓዴ አሻራ ልማት ጋር እንዲተሳሰር መደረጉንም ተናግረዋል።

በዚህም አርሶ አደሩ ከሰብል ልማቱ ጎን ለጎን በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርቶ ተጨማሪ ገቢ እያገኘ መሆኑን የገለጹት አቶ አዳሙ፣ ኢኒሼቲቩ ለአርሶ አደሩ የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርዓት እንዲኖር ከማድረግ ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራም ማገዙን ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ 20ሺህ ቶን የማር ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደሥራ መገባቱን ገልጸው፣ በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ከ12 ሺህ ቶን በላይ ማር ለገበያ መቅረቡን ተናግረዋል።

የማር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም ከ190ሺህ በላይ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ለአርሶ አደሮች ተደራሽ መደረጉንም ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ  በዞኑ በንብ ማነብ ሥራው 36 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እና ወጣቶች እየተሳተፉ ሲሆን ምርታማነትና ገቢያቸውን እንዲያሳድጉም የባለሙያ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው።


 

በዞኑ በንብ ማነብ ሥራ ከተሰማሩ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ዮሐንስ ጌታቸው ከ200 በላይ ዘመናዊ ቀፎ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የማር ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ በዓመት እስከ 500 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከሰብል ልማት በተጓዳኝ በሚያከናውኑት የንብ ማነብ ሥራ ገቢያቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ዋኬኔ አብዲሳ እና አቶ ደጀኔ ግዛው የተባሉ ነዋሪዎች ናቸው።


 

በንብ ማነብ  ሥራው  ውጤታማ  እንዲሆኑ ከዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ዘመናዊ የንብ ቀፎ እና ሙያዊ ድጋፍ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።

በኢሉባቦር ዞን ከአምስት ዓመት በፊት 9 ሺህ 280 ብቻ የነበረው ዘመናዊ ቀፎ የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቪ ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት ከ366 ሺህ በላይ መድረሱን ከዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም