ዩኒቨርሲቲው ሳይንሳዊ የብዝሃ ደን ልማት ስራን የሚደግፍ የዘር ባንክ ሊያቋቁም ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ሳይንሳዊ የብዝሃ ደን ልማት ስራን የሚደግፍ የዘር ባንክ ሊያቋቁም ነው
ጎንደር፤ ግንቦት 4/2018 (ኢዜአ)፡- ጎንደር ዩንቨርሲቲ ሳይንሳዊ የብዝሃ ደን ልማት ስራን የሚደግፍ ሀገር በቀል የደን ዛፎች የዘር ባንክ ለማቋቋም የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።
በዩኒቨርሲቲው የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የደን ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አስማማው ዓለሙ (ዶ/ር) እንደገለጹት የሚቋቋመው የዘር ባንክ የሚስተዋለውን የደን ዘር ጥራትና አቅርቦት ችግር የሚፈታ ነው።
የዘር ባንኩ መቋቋም ችግኞች ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚነታቸውን በምርምር በማረጋገጥ የጽድቀት መጠናቸውን ለማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።
በተጨማሪም በሽታን፣ ተባይንና ድርቅን በመቋቋም ከአካባቢው ጋር በፍጥነት ተላምደው ውጤታማ መሆን የሚችሉ የደን ዛፍ ዝርያዎችን ለማቆየት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
የዘር ባንኩ በምርምር ጣቢያዎች ተሞክረውና የጥራት ደረጃቸው በቤተ -ሙከራ ተፈትሾ ያለፉ የደን ዛፍ ዘሮችን በሳይንሳዊ መንገድ ጠብቆ ለማቆየት አጋዥ ሚና ይጫወታል ሲሉም አክለዋል።
በዚህም የሀበሻ ጽድ፣ የኮሶ ዛፍ፣ ዋንዛ፣ ወይራና የአካሽያ ግራር የመሳሰሉ የደን ዛፎችን በሳይንሳዊ መንገድ በመንከባከብ ዘር የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁን በተሰራው ስራም 13 አይነት የዛፍ ዝርያዎችን በማላመድ በአሁኑ ወቅት 254 ኪሎ ግራም ዘር በከተማዋ በተቋቋሙ የችግኝ ጣቢያዎች እንዲፈሉ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
በተጨማሪም በከተሞች የኮሪደር ልማት የአረንጓዴ የጥላ ዛፍ ችግኞችን ለማቅረብ የሚያስችል ሰርቶ ማሳያ በማቋቋም ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በአካባቢው ጥራት ያለው ዘር አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ ባለመኖሩ ለደን ልማት ስራው እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ካህሌ ጀንበር (ዶ/ር) ናቸው፡፡
የዘር ባንኩ መቋቋም እንደ ሀገር እየተካሄደ የሚገኘውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስኬታማና ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡