በክልሉ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት ምቹ ምህዳር ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት ምቹ ምህዳር ተፈጥሯል
ሐረር፤ ግንቦት 4/2018(ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተፈጠረው ምቹ ምህዳር ውጤታማ ስራ መስራት እንዳስቻላቸውና በምርጫ ሂደቱ ላይ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
ፓርቲዎቹ በተለይም የምርጫ ዝግጅቱ ፍትሃዊ እና አካታች በሆነ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ተዓማኒ እንዲሆን እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የሐረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) የክልሉና የድሬዳዋ አስተባባሪ ወይዘሮ ሐሰነት ሙሜ፤ የተፈጠረው ሰፊ የምርጫ ውድድር ምህዳር እና የጋራ ምክር ቤቱ ፓርቲዎች በምርጫ ሂደቱ በንቃት እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።
ፓርቲዎቹ በተለይም በመገናኛ ብዙሃን በኩል የተሰጣቸውን ዕድል በመጠቀም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙና እስካሁንም በሚያከናውኑት ማንኛውም እንቅስቃሴ ምንም ዓይነት ችግር እንዳልገጠማቸው አስታውቀዋል።
መራጩ ህዝብ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ ከማድረግ አንጻር በጋራ ምክር ቤት መሰረት ሰፊ ስራ መስራታቸውን የተናገሩት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዳይሬክተር ሐሰን አብዲ ናቸው።
የምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሁሉም ፓርቲዎች አማራጭ ሐሳቦቻቸውን ነጻና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለመራጩ ህዝብ እያስተዋወቁ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የሐረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ እና የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) የክልሉ ምክትል ሰብሳቢ አብዱልሃፊዝ አህመድ ፓርቲያቸው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁን በሚያከናውኑት የቅድመ ምርጫ ስራዎች ፓርቲያቸው ያለምንም እንከን እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በክልሉ የምርጫ ቅስቀሳቸውን በተለያዩ አማራጮች በሰላማዊ ሁኔታ እያከናወኑ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በሐረሪ ክልል በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለክልል ምክር ቤት በግል የሚወዳደሩት ጀማል አባጋሮ አህመድ ናቸው።