የዓለም አትሌቲክስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጆን ሪጅን በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም አትሌቲክስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጆን ሪጅን በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 4/2018 (ኢዜአ)፦ የዓለም አትሌቲክስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጆን ሪጅን በያዝነው ሳምንት በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ያደርጋሉ።
የቀድሞ የእንግሊዝ አትሌት ጆን ሪጅን ከዓለም አትሌቲክስ የጨረታ፣ ውድድርና ኩነቶች መምሪያ ኃላፊ ማርክ ኸርስት (Mark Hurst) ጋር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በአዲስ አበባ በመገንባትና በመስፋፋት ላይ ያሉ የአትሌቲክስ መሠረተ ልማቶችን እንደሚጎበኙ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በቀጣይ ልታስተናግዳቸው በጠየቀቻቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች ዙሪያ ከተለያዩ የመንግሥት እና የፌደሬሽኑ አመራሮች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉም ገልጿል።
ይህ ጉብኝት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ መድረክ ያላትን ከፍተኛ ስፍራ የሚያጠናክር እና ወደፊት ትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ ያላትን አቅም እንደሚያሳይ ፌዴሬሽን አመልክቷል።
የመጀመሪያው የዓለም አትሌቲክስ የአንድ ቀን ውድድር (አዲስ አበባ ግራንድ ፕሪክስ) በአዲስ አበባ ስታዲየም መካሄዱ የሚታወስ ነው።
የዓለም አትሌቲክስ የኢትዮጵያን የማስተናገድ አቅም በመመልከት በነሐስ ደረጃ የተደረገው ውድድር ከእ.አ.አ 2027 አንስቶ በወርቅ ደረጃ እንዲካሄድ መወሰኑም አይዘነጋም።