የመውረድ ስጋት ያለበት ቶተንሃም ከሊድስ ዩናይትድ አቻ ተለያየ - ኢዜአ አማርኛ
የመውረድ ስጋት ያለበት ቶተንሃም ከሊድስ ዩናይትድ አቻ ተለያየ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 4/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 36ኛ ሳምንት ቶተንሃም ሆትስፐርስ እና ሊድስ ዩናይትድ ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
በቶተንሃም ሆትስፐርስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ማቲስ ቴል በ50ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ጎል ቶተንሃም መሪ ሆኗል።
ዶምኒክ ካልቨርት-ሉዊን በ74ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ያሳረፈው ጎል ሊድስ ዩናይትድን አቻ አድርጓል።
በሊጉ ያስቆጠረውን ጎል ብዛት ወደ 13 ከፍ አድርጓል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ቶተንሃም፣ በሁለተኛው የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ሊድስ ዩናይትድ የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገዋል።
ለረጅም ወራት በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቆ የነበረው የቶተንሃም አማካይ ተጫዋች ጀምስ ማዲሰን ወደ ሜዳ ተመልሷል።
ውጤቱን ተከትሎ ቶተንሃም ሆትስፐርስ በ38 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዟል። 18ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ዌስትሃም ዩናይትድ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ አሁንም የመውረድ ስጋት አለበት።
በሊጉ መቆየቱን ያረጋገጠው ሊድስ ዩናይትድ በ44 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል።
ከቶተንሃም ሆትስፐርስ እና ዌስትሃም ዩናይትድ ማን በሊጉ ይቆያል? ማን ይወርዳል? የሚለው ጉዳይ አጓጊ ሆኗል።
ጨዋታውን ተከትሎ 36ኛ ሳምንት ተጠናቋል።
የ37ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ከግንቦት 7 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ ይካሄዳል።