ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አሠራሩን ለማዘመንና ተወዳዳሪ ለመሆን እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አሰራሩን በማዘመን ከወቅቱ ጋር ለመዘመንና ተወዳዳሪ ለመሆን እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለፀ።

ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን የ2018 በጀት ዓመት የ9 ወራት የበጀት አፈፃፀምንና የ2019 በጀት ዓመት እቅድን ገምግሟል።


 

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አመራሮች እንደገለጹት፤ ድርጅቱ ላለፉት 85 ዓመታት የኢትዮጵያን ታሪክ በጽሑፍም በፎቶ ግራፍም ሰንዶ የያዘ አንጋፋ ተቋም ነው፡፡


 

በድርጅቱ የዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኤፍሬም ተክሌ፤ በአሁኑ ወቅት ዲጂታል ሚዲያው ለህትመት ሚዲያው ፈታኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ድርጅቱም የዲጂታል ሚዲያውን መስፋፋት ታሳቢ አድርጎ እዩሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በህትመትም በዲጂታልም ተወዳዳሪና ተደራሽ ለመሆን ለዲጂታል አሰራሮች ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል፡፡ 


 

የድርጅቱ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወንድም ተክሉ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ የራሱ የጋዜጣ እና መጽሔት ህትመት ቤት አለመኖሩ ለሥራው ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነበት ተናግረዋል፡፡

ይህ በተደጋጋሚ ሲነሳ የቆየ ችግር መሆኑን አንስተው፤ የጋዜጣና የመፅሔት ህትመት የየራሳቸው ባህሪ፣ ጥራትና ደረጃ የሚጠይቁ በመሆናቸው በተለያዩ ማተሚያ ቤቶች ለማሳተም እንደሚገደድ ጠቁመዋል።

ለሁለቱም ህትመቶች የሚሆኑ ማተሚያ ቤቶች እንዲኖረው ቢደረግ የድርጅቱን አሠራር እንደሚያሻሽልና ወጪን እንደሚቀንስ ጠቅሰዋል።

ከዚህም ባለፈ ለሌሎች ድርጅቶች ጭምር የህትመት አገልግሎት በመስጠት የገቢ ምንጭ ማድረግ እንደሚችልም አንስተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ብዝኃነትን መሰረት ያደረገ የህትመት አቅምን ለማሳደግ እያደረገ ያለውን የሪፎም ሥራ አድንቀዋል።

ድርጅቱ ከወቅቱ ጋር ለመዘመንና ተወዳዳሪ ለመሆን እያደረገ ያለው ተግባር የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል።

የድርጅቱ ማተሚያ ቤት ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ምክክር እንደሚደረግበትና እንደሚታይ ጠቁመዋል።

ተቋሙ አሠራሩን ለማሻሻልና የገቢ አቅሙን ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም