ቀጥታ፡

በክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል በሚከናወኑ ተግባራት ውጤት እየተገኘ ነው

ሀዋሳ፤ ግንቦት 3/2018(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል በሚከናወኑ ተግባራት ውጤት እየተገኘ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በክልሉ ሎካ አባያና ደራራ ወረዳዎች በበልግ ወቅት በኩታ ገጠም እየለማ የሚገኘውን የበቆሎ ማሳ በመስክ ተመልክተዋል።




ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ የሰብል ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ገበያን የሚያረጋጋ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ውጤት እየተገኘ ነው።

በዚህም በበልግ ወቅት ፆም የሚያድር መሬት እንዳይኖር በማድረግና ግብዓቶችን በወቅቱ በማቅረብ እየተከናወነ ባለው የእርሻ ስራ የምርት ቁመናው ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በበልጉ ያለውን አመቺ የዝናብ ስርጭት እንዲሁም የቴክኖሎጂ አቅርቦት በመጠቀም የተሻለ ምርት ለማግኘት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት አሁን ላይ ለማሳ እንክብካቤ ስራ ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።

በክልሉ ያለውን የእርሻ አቅም አሟጦ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና በምግብ ራስን የመቻል ግብን ለማሳካት የሚደረጉ ጥረቶች ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመው ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በበልግ ወቅት በክልሉ በሰብል የሚለማ የመሬት መጠን እያደገ መምጣቱን ገልጸው፣ አብዛኛው መሬት በምርጥ ዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።




የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሃላፊ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው በክልሉ በበልግ እርሻ ከ152 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ዋና ዋና ሰብሎች እንዲሁም በስራስርና አትክልቶች መሸፈኑን ተናግረዋል።

አጠቃላይ ከለማው መሬትም ከ24 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።




በልማቱ እየተሳተፉ ካሉ መካከል በሎካ አባያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ጽጌ ኩማ እንደገለጹት የአካባቢው 80 አርሶ አደሮች ከ75 ሄክታር በላይ ኩታ ገጠም መሬት ላይ በቆሎ እያለሙ መሆናቸውንና የማሳ እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።




ሌላው በዳራራ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ዳዊት ብንኦ 40 ሆነው በኩታገጠም በቆሎ እያለሙ መሆናቸውን ጠቁመው ምርቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝና በጋራ መስራታቸው ውጤታማ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም