ኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ቋሚ የሁለትዮሽ ምክክር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ቋሚ የሁለትዮሽ ምክክር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ቋሚ የሁለትዮሽ የምክክር ማዕቀፍ ስምምነት በዋሽንግተን ዲሲ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እና በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የፖለቲካ ጉዳዮች አሊሰን ሁከር ፈርመዋል።
በዚህ ስምምነት ኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ይበልጥ የሚያጠናክሩ የጋራ ትግበራ የሚሹ የትብብር አድማሶችን በማስፋት በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል።
የተፈረመው የሁለትዮሽ መዋቅራዊ ምክክር በየዓመቱ አንዴ አዲስ አበባ ሌላ ጊዜ ዋሽንግተን ዲሲ የሚካሄድ ሲሆን የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስብሰባውን በጋራ የሚመሩት ይሆናል።
ኢትዮጵያ እና አሜሪካ የሁለትዮሹ መዋቅራዊ ምክክር ሦስት ምሰሶዎችን ያካተተ እንዲሆን ተስማምተዋል።
አንደኛው የኢኮኖሚ ብልጽግናን፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት የሚዳስስ ሲሆን በዚህ ክፍል የሁለትዮሹን ኢኮኖሚያዊ እና የንግድ ትስስር የበለጠ ማጠናከርና ኢንቨስትመንት እና ንግድን ለማስፋት እንደሚሰራ ተገልጿል።
ሁለተኛው የመከላከያ እና ጸጥታ ትብብርን የሚመለከት እንደሆነና የጸጥታ ጉዳይ ትብብርን ማጠናከርና በጋራ የደኀንነት ጉዳዮች ዙሪያ ተሳትፎን ማጠናከርን ያካትታል።
የመጨረሻው እና ሦስተኛው ምሰሶ ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን የተመለከተ ሲሆን በዚህ ክፍል የጋራ ጥቅምን እንዲሁም ቀጣናዊ ሰላምንና ደኀንነትን የሚያስጠብቁ አካሄዶችን በመፈተሽና በትብብር መሥራትን ያረጋግጣል።
ይህ ቋሚ የሁለትዮሽ ምክክር ማዕቀፍ ስምምነት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ዘላቂ በሆነ መንገድ የሚያስቀጥልና የሚያጠናክር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።