ለተቃና ነገ የኢትዮጵያ ትጋት አንዱ መገለጫ - ኢዜአ አማርኛ
ለተቃና ነገ የኢትዮጵያ ትጋት አንዱ መገለጫ
(በዮሐንስ ደርበው)
ኢትዮጵያ ከምትከውናቸው ዐበይት ጉዳዮች መካከል ሰው ተኮር ተግባራት ቀዳሚው ነው። በአዲስ አበባ በተካሄደው ዓለምአቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባዔ፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢትዮጵያ ለልማት በምታደርገው ጥረት ሰው ተኮር የልማት አቅጣጫ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ነው ብለዋል። መንግሥት መጪው ትውልድ ጤናማ፣ ብቁ እና ውጤታማ እንዲሆን የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራምን ማዕከል አድርጎ ሁሉን አቀፍ ሥራ እየተገበረ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
በዚህም መሠረት፤ የልጆች ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት፣ የምገባ ሥርዓትን ማሳደግ፣ የሕጻናት መጫወቻ ሥፍራዎች ግንባታ ላይ ተጨባጭ ውጤቶች መምጣታቸውንም ነበር የጠቀሱት። ሀገር አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ልማትና ትምህርት ፖሊሲ የዘላቂ ብልጽግና መንገዳችን ከሆነው የመደመር ዕሳቤ ጋር በተናበበ መልኩ እየተተገበረ በስኬት ቀጥሏልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለነገ የተዘጋጀ ትውልድ ለመገንባት በሕግና በፖሊሲ የተደገፉ የቀዳማይ ልጅነት ኢኒሼቲቮችን እየተገበረች እንደምትገኝም አስታውቀዋል። ለአብነትም፤ በ2015 ተሻሽሎ የፀደቀው ሀገር አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ልማት እና ትምህርት የፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲሁም በ2017 የፀደቀውን አጠቃላይ የትምህርት አዋጅ መሠረት በማድረግ ከ35ሺህ በላይ የቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመላው ሀገሪቱ እየተተገበረ መሆኑን አንስተዋል።
በመንግሥት ተቋማት የሕጻናት ማቆያ ማዕከላት ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን በመጠቆምም፤ ኢትዮጵያ የሕጻናትን ደኅንነት ማሻሻል የሚያስችል ጉልኅ ብሔራዊ መርሐ-ግብር መጀመሯን አንስተዋል። በሰቆጣ ቃል ኪዳን አማካኝነት የ15 ዓመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ከሁለት ዓመት በታች በሆኑ ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን መቀንጨር በ2022ዓ.ም ዜሮ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት።
የሌማት ትሩፋትና የአልሚ ምግቦች ምርታማነት የሕጻናትን ጉዳት ለመቀነስና የልጆችን ጤናማነት መጨመር እያስቻሉ እንደሚገኙም ነው የተናገሩት። ኢትዮጵያ ለዘላቂ የልማት ግቦችና ለሕጻናት መብቶች ጥበቃ የገባቻቸውን ቃል ኪዳኖች ወደ ተግባር እየለወጠች መሆኑን በማንሳት፤ ይህንንም አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
መንግሥት ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተቀናጀ የቀዳማይ ልጅነት ልማትን በመላ ሀገሪቱ ለማስፋት ሙሉ ቁርጠኛ መሆኑንም አመላክተዋል። በዚህም መሠረት፤ በጀት በመመደብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል፣ የተማሪዎችን ምገባ በማስፋፋት ውጤት ማምጣቱን ነው የሚያብራሩት።
ልጆች በአካልና በመንፈስ የሚጎለብቱባቸው የስፖርትና የመዝናኛ ቦታዎች በየአካባቢው በመገንባት፣ በኮሪደር ልማት ለልጆች ምቹ ሥፍራ እየተፈጠረ መሆኑንም በመጥቀስ። ልጆች ላይ መሥራት በነገ ሀገር፣ አኅጉር እና ዓለም ላይ መሥራት በመሆኑ በትጋት ማስቀጠል እንደሚገባም በአጽንኦት ይናገራሉ።
አፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ተግዳሮቶችን ለመፍታት የራሷን መፍትሔዎች በማፍለቅ፣ በብሔራዊ የልማት አጀንዳዋ እያካተተች መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ከበደ ወርቁ ናቸው።
በሕጻናት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ማንኛውም ሀገር በመጪው ትውልድ ላይ ሊያደርጋቸው ከሚችላቸው እጅግ አስፈላጊ ኢንቨስትመንቶች አንዱ መሆኑንም ያነሳሉ። አፍሪካ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ላይ ያሉባትን ተግዳሮቶች ከመጋፈጥ ባለፈ፤ የራሷን መፍትሔዎች እያመነጨች መሆኑንና ጉዳዩን የብሔራዊ ልማት አጀንዳዋ አካል እያደረገችው እንደምትገኝም ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ይህን ዓለምአቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባዔ እንድታስተናግድ የተመረጠችበት ዋና ምክንያትም፤ በዘርፉ እያከናወነች ያለው ተግባር አርዓያነት ያለው በመሆኑ ነው ብለዋል። ከተማዋ የጤና እና የሥርዓተ-ምግብ አገልግሎቶችን ያካተተ የተቀናጀ ዘርፈ-ብዙ አሠራር መዘርጋቷን ጠቅሰው፤ የቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት እና የቀን የሕጻናት እንክብካቤ ማዕከላትን በከተማ አቀፍ ስትራቴጂ ተግባራዊ እያደረገች እንደምትገኝም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ መዲናዋ በቀዳማይ ልጅነት ያመጣችው ተጨባጭ ውጤት በአርዓያነት እንድትጠቀስ እንዳደረጋት አንስተዋል። በሕጻናት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ዓመታት የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች፤ በትምህርት፣ በሰው ሃብት ልማትና በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ረጅም ጊዜ የሚቆይ ፋይዳ እንዳለውም አስረድተዋል።
በዚህም በአዲስ አበባ ፍትሐዊና አካታች የቀዳማይ ልጅነት ልማት መርሐ-ግብርን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ የትውልድ ግንባታ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል። "ሕጻናት የአዲስ አበባ የነገ ተስፋዎች" የሚል ፍኖተ ካርታ በመቅረጽ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ለሚሆኑ ከስድስት ዓመት በታች ሕጻናት ሁለንተናዊ ዕድገት መረጋገጥ እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በትምህርት ቤት ምገባ መርሐ-ግብርም ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ፣ ዩኒፎርምና በቀን ሁለት ጊዜ ምግብ በማቅረብ በሕጻናት ክብካቤ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል ነው ያሉት። የሕጻናት ማቆያና መጫወቻ የመሠረተ-ልማት ግንባታ፤ ሕጻናት ነፃ የሕክምና፣ የምገባና የሥነ-ልቦና አገልግሎት የሚያገኙበትን ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል።
የቀዳማይ ልጅነት መርሐ-ግብር በ2015 ዓ.ም ሲጀመር በዕድገት ወደ ኋላ የቀሩ የሕጻናት መጠን ከነበሩበት 13 በመቶ አሁን ላይ ወደ 10 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ከንቲባዋ አመላክተዋል። አክለውም፤ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዝግጁነታቸው ከነበረበት 49 በመቶ አሁን ወደ 90 በመቶ ማደጉንም ተናግረዋል።
ሀገር በሁሉም ዘርፍ የበቃ መጪ ትውልድ እንዲኖራት መንግስት የያዘው ጥረት በሚፈለገው መጠን ለውጤት እንዲበቃ የሁሉንም ትኩረትና ተሳትፎ ይሻል። ለነገ በሁሉም ዘርፍ የዳበረ ትውልድና የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን መሆን ዛሬ ላይ እየተደረገ ያለው ርብርብ የሀገራችንን መፃኢ ብሩህ ተስፋ ይበልጥ የሚያለመልም ነውና ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።