ቀጥታ፡

ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራትን በጥናትና ምርምር ማገዝ ይገባል

ወራቤ፤ ግንቦት 3/2018(ኢዜአ)፡- ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራትን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር ማገዝ እንዳለባቸው ተገለጸ።

"የምርምርና የፈጠራ ሥራን ለዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት" በሚል መሪ ሀሳብ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ በወራቤ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት የሚከናወኑ ተግባራትን ስኬታማ ለማድረግ ወሳኝ መሆናቸውም ተመላክቷል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ቶፊቅ ጀማል (ዶ/ር) በዚሁ ወቀት እንዳሉት በጥናትና ምርምር የታገዘ የልማት ሥራ ቀጣይነት ላለው እድገት ወሳኝ ነው።

እንደሀገር ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት በመንግስት የሚከናወኑ ተግባራትን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር በማገዝ ስኬታማ ለማድረግ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ወራቤ ዩኒቨርሲቲ እንደሀገር ዘላቂ የልማት ግቦችን ስኬታማ ለማድረግ የሚከናወኑ ሥራዎችን በጥናትና ምርምር በማገዝ የበኩሉን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

መንግስት ለዲጂታል ቴክኖሎጂ የሰጠውን ትኩረት ለማገዝም ዩኒቨርሲቲው ከደቡብ ኮሪያው "ዮንግናም ዩኒቨርሲቲ" ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ተማሪዎችን ተቀብሎ እያሰለጠነ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ዛሬ የተጀመረው ዓለም አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስም ተሞክሮ የሚገኝበት ከመሆኑ ባለፈ በዩኒቨርሲቲው እየተከናወኑ ያሉ የምርምር ሥራዎችን ተወዳዳሪነት ከፍ ለማድረግ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ረዳት ፕሮፌሰር አንዋር አህመድ በበኩላቸው እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በቢዝነስ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ መስኮች ላይ ያተኮሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

የዓለም አቀፍ የምርምር ኮንፍረንሱ በዩኒቨርሲቲው መካሄድ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስፋፋት ካለው ፋይዳ በተጨማሪ እርስ በርስ ተሞክሮ ለመለዋወጥ ያስችላል ብለዋል።

በመድረኩ ተገኝተው የምርምር ሥራቸውን ያቀረቡት በጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ድልነሳው የኋላው እንደገለፁት፣ ስኬቶችን ለማጠናከርና ተግዳሮቶችን ለመፍታት በምርምርና በፈጠራ የታገዙ ሥራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል።

በአስተማማኝና ዘላቂ ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት ውስጥ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ሥራ ለመስራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና  የጎላ መሆኑን አስታውቀዋል።

የምርምር ኮንፍረንሱ ለሀገር የሚጠቅሙ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎችን ለመቀመር እንደሚያስችል የተናገሩት ደግሞ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመጡት መምህርና ተመሪማሪ ጋዲሳ አዳሙ ናቸው።

ለሦስት ቀናት በሚቆየው መድረክ ከሀገር ውስጥና ከውጪ የመጡ 43 ተመራማሪዎች የምርምር ሥራዎቻቸውን በማቅረብ  የልምድ ልውውጥ እንደሚደረግ ታውቋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም