ቀጥታ፡

በፓርቲው መሪነት ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ባህርዳር፣ደሴ፣ገንዳ ውሃ ፤ግንቦት 3/2018 (ኢዜአ)፡- በብልፅግና ፓርቲ መሪነት  ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።

የብልፅግና ፓርቲ "ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር" በሚል መሪ ሀሳብ የምርጫ ማኒፌስቶውንና የዕጩዎች ትውውቅ መድረኩን  በባህርዳር፣ ደሴና ገንዳ ውሃ ከተሞች   አካሂዷል።


 

‎በብልጽግና ፓርቲ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ሁሴን በመድረኩ ላይ እንደገለጹት  በፓርቲው መሪነት በከተማዋ ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተካሂደዋል ።

የጣና ዳር አረንጓዴ ልማትና የኮሪደር ልማት፤ የአባይ ድልድይ እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ የአስፋልት መንገዶችና ሌሎች የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

ይህም ከተማዋን ለቱሪዝም፣ ለንግድና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።

 ፓርቲው በቀጣይም መሰል የልማት ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።


 

በተያያዘ ዜና በብልጽግና ፓርቲ የደሴ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ አለማየሁ በመድረኩ እንደገለፁት፣ የብልጽግና ፓርቲ ዘመን ተሻጋሪ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።


 

የልማት ፕሮጀክቶችን  አጠናክሮ ለማስቀጠል የምርጫውን ሰላማዊነት ማረጋገጥ ላይ በማተኮር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፣ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ዳር ለማድረስ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል  የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የአስተዳደር ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጥላሁን መኳንንት በገንዳ ውሃ ከተማ በተካሄደ መድረክ ላይ እንደገለጹት ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግስት ክትትልና ድጋፍ እያደረገ ነው። 


 

ምርጫው  የህዝብ ድምፅ የሚከበርበትና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም