ቀጥታ፡

ብልጽግና ፓርቲ በመደመር እሳቤ በሰው ተኮር የልማት ሥራዎች ውጤት አስመዝግቧል  

ሳጃ፤ ግንቦት 3/2018 (ኢዜአ)፦ብልጽግና ፓርቲ በመደመር መንግስት እሳቤ ጠንካራ ተቋማት በመገንባትና በሰው ተኮር የልማት ሥራዎች ውጤት ማስመዝገቡን በፓርቲው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ፓርቲው "ኢትዮጵያ ወደ ተምሳሌት ሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ አባላቱና ደጋፊዎቹ በተገኙበት ዛሬ በየም ዞን ሳጃ ከተማ የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሂዷል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ፓርቲው  በለውጡ ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት ለህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ ሰጥቷል።

በመደመር መንግስት እሳቤ በመመራት ጠንካራ ተቋማትን ከመገንባት ባለፈ የተለያዩ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን አከናውኗል ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል ለዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ አበክሮ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሺመልስ እጅጉ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ዞኑ በለውጡ ዓመታት የአካባቢውን  ጸጋዎች ከሰው ኃይል ልማት ጋር አቀናጅቶ ባከናወናቸው የልማት ሥራዎች በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል።


 

በዚህም በመሰረተ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት እና በአትክልት ልማት ከመቼውም ጊዜ በላይ ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ እንደ ሀገር ላቀዳቸው የልማት ግቦች መሳካት ህዝቡ ከፓርቲው ጎን በመሰለፍ በጠቅላላ ምርጫው ይሁንታውን እንዲሰጠውም ጥሪ አቅርበዋል።

በምርጫ ቅስቀሳው ከተሳተፉት መካከል አቶ ንጉሴ ራያ እና የደሪ ዙርያ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ብርቱካን ሙራስ እንዳሉት፤ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች በተሰሩ ሥራዎች የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እያደገ መጥቷል።


 

የብዙ ጊዜ ጥያቄያቸው የነበረው የዞን መዋቅር ምላሽ ማግኘቱን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ በአካባቢው ስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በስፋት በማምረት ኢኮኖሚያዊ እድገት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል ።

በተለይም በሳጃ ከተማ የተከናወኑ የኮሪደር፣ የመንገድ፣ የወጣቶች መዝናኛ እና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለማስቀጠል  ከፓርቲው ጎን በመሆን እንደሚንቀሳቀሱም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም