በክልሉ ዲጂታል ኢትዮጵያን ለማሳካት ትምህርት ቤቶችን መሰረት ያደረጉ ሥራዎች ተጀምረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ዲጂታል ኢትዮጵያን ለማሳካት ትምህርት ቤቶችን መሰረት ያደረጉ ሥራዎች ተጀምረዋል
ባህር ዳር፤ ግንቦት 3/2018 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ዲጂታል ኢትዮጵያን ለማሳካት ትምህርት ቤቶች ላይ መሰረት ያደረጉ ሥራዎች መጀመራቸውን የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው የተማሪዎችና የትምህርት ቤቶች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስልጠናና ውድድር አካሂዷል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ የውድድሩ አስተባባሪ አቶ ሃብታሙ ላቀ እንደገለጹት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት በማድረግ እየተሰራ ነው።
ለተግባራዊነቱም ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራን ለማሳደግ ስልጠናዎችና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ፕሮጀክት ውድድር በማድረግ ልምድ የሚቀስሙበትን አውድ ለማስፋት መሰራቱን ጠቁመዋል።
የእዚሁ አካል የሆነውና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ፕሮጀክት ተወዳድረው ከ1 እስከ 3 በመውጣት የላቀ ውጤት ላስመዘገቡት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት መስጠቱንም አስረድተዋል።
ማበረታቻውም ተማሪዎችና ትምህርት ቤቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ አተኩረው በመስራት የዲጂታል ኢትዮጵያ ግቦችን ለማሳካት የላቀ ተነሳሽነት እንዲኖራቸው ያስችላል ብለዋል።
በቢሮው የኤሌክትሮኒክስ መንግስት አገልግሎት ቡድን መሪና የውድድሩ ዳኛ አቶ ደጀኔ ብርሃኔ በበኩላቸው የተማሪዎችን የቴክኖሎጂ እውቀት በማሳደግ ችግር ፈች ሥራዎችን ለማህበረሰቡ እንዲያቀርቡ መሰራቱን ጠቁመዋል።
ለውድድሩ የቀረቡት ፕሮጀክቶችም የዚሁ ሥራ አካል መሆናቸውን ጠቁመው፣ መመዘኛዎቹ የፈጠራ ጽንሰ ሃሳብ ችግር ፈችነት፣ የፈጠራው አተገባበር ጥራት፣ አረዳድና አቀራረብ ላይ መስረት ያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ውድድሩ ተማሪዎች በቀጣይ በቴክኖሎጂና በመካኒካል የፈጠራ ሥራዎች የጀመሯቸውን ተግባራት ዳር በማድረስ ለአገር ጥቅም እንዲያውሉና ሌሎች ተማሪዎችም የእነሱን ፈለግ እንዲከተሉ መነሳሳት የፈጠረ ነው ብለዋል።
ከካቶሊክ ትምህርት ቤት የመጣው የ10ኛ ክፍል ተማሪ ቅዱስ አላምረው የግብርናውን ዘርፍ ችግር የሚፈታ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤት በማቅረብ 1ኛ በመውጣት ተሸልሟል።
የፈጠራ ሥራው ለአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ገልጾ ይህም የመሬት ለምነት፣ የአየር ጸባይን እና የዝናብ ሁኔታን በመለየት ምን አይነት ሰብል መዘራት እንዳለበት መረጃ የሚሰጥ መሆኑን ነው የገለጸው።
የጣና ሃይቅ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አብርሃም ዮሴፍ በበኩሉ በውድድሩ “የቤት ጥበቃ ሲስተም” የፈጠራ ስራ በማቅረብ 2ኛ ደረጃን አግኝቶ መሸለሙን ገልጿል።
ፕሮጀክቱም በመኖሪያ ቤት ላይ የሚደርስን በጭስ መታፈን፣ የእሳት አደጋ፣ የስርቆት ወንጀልና ሌሎች አደጋዎችን ለመከላከል የሚያስችል ነው ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪ የመኖሪያ ቤትን ሙቀት መጥኖ በመቆጣጠር የነዋሪዎችን ጤንነትና ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችል መሆኑን ጠቁሞ ፕሮጀክቱ በቀላሉ የሚተገበርና አዋጭ መሆኑን ገልጿል።
ለሦስት ቀናት በተካሄደው የስልጠናና የውድድር መድረክ ከሰባት ትምህርት ቤቶች የመጡ ተማሪዎች 19 የፈጠራ ፕሮጀክቶችን ያቀረቡ ሲሆን በውድድሩ ከ1 እስከ 3 ለወጡትም ቢሮው የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል።