ቀጥታ፡

የቀዳማይ ልጅነት የልማት መርሃ ግብር አዲስ አበባን አፍሪካዊት የትውልድ ግንባታ ተምሳሌት ከተማ እያደረጋት ነው 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2018 (ኢዜአ)፦የቀዳማይ ልጅነት የልማት መርሃ ግብር አዲስ አበባን አፍሪካዊት የትውልድ ግንባታ ተምሳሌት ከተማ እያደረጋት መሆኑን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ''አፍሪካ በቀዳማይ ልጅነት ሥርዓት ለውጥ የግንባር ቀደምትነት ሚና፤ ከአካባቢያዊ ሞዴሎች ወደዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ” በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀውን አዲስ ዓለም አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤን በይፋ ከፍተዋል።


 

በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ መዲናዋ በቀዳማይ ልጅነት ያመጣችው ተጨባጭ ውጤት በአርዓያነት እንድትጠቀስ አድርጓታል ብለዋል።

ከፅንስ እስከ ስድስት ዓመት የዕድሜ ክልል የሚደረግ ስኬታማ ኢንቨስትመንት አዲስ አበባን የአፍሪካ ተመራጭ የህፃናት ማሳደጊያ ከተማ እያደረጋት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ለሕፃናትና እናቶች ምቹ ምኅዳር መፍጠር ለቤተሰብ፣ ማህበረሰብና ለሀገር ዘላቂ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ተናግረዋል።

በሕፃናት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ዓመታት ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች በትምህርት፣ በሰው ሃብት ልማትና በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ረጅም ጊዜ የሚቆይ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰዋል።

በዚህም በአዲስ አበባ ፍትሐዊና አካታች የቀዳማይ ልጅነት የልማት መርሃ ግብርን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ የትውልድ ግንባታ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።

"ሕፃናት የአዲስ አበባ፤ የነገ ተስፋዎች" የሚል ፍኖተ ካርታ በመቅረፅ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ለሚሆኑ ከስድስት ዓመት በታች ሕፃናት ሁለንተናዊ ዕድገት መረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ፍኖተ ካርታውም የተቋማትን ቅንጅት በማሰናሰል የተቀናጀ የቀዳማይ ልጅነት ልማት አገልግሎት በሁሉም የመንግስት ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች በመደበኛነት እንዲሰጥ አስችሏል ብለዋል።

በትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብርም ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ፣ ዩኒፎርምና በቀን ሁለት ጊዜ ምግብ በማቅረብ በሕጻናት ክብካቤ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።

የሕፃናት ማቆያና መጫወቻ የመሰረተ ልማት ግንባታ ውጤቶችም ሕፃናት ነፃ የሕክምና፣ የምገባና የሥነ-ልቦና አገልግሎት የሚያገኙበትን ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል።

የቀዳማይ ልጅነት መርሃ ግብር በ2015 ዓ.ም ሲጀመር በዕድገት ወደ ኋላ የቀሩ የሕፃናት መጠንን ከነበረበት 13 በመቶ አሁን ላይ ወደ 10 ነጥብ 9 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዝግጁነታቸው ከነበረበት 49 በመቶ አሁን ላይ ወደ 90 በመቶ ማሳደግ እንደተቻለም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም