የስፖርቱ ዘርፍ አንድነትንና አብሮነትን በማጠናከር ረገድ የማይተካ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርቱ ዘርፍ አንድነትንና አብሮነትን በማጠናከር ረገድ የማይተካ ሚና አለው
ጋምቤላ፤ ግንቦት 3/2018 (ኢዜአ)፦ ስፖርት ከሚያስገኘው ዘርፈ-ብዙ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር፣ የሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከርና የወንድማማችነት መንፈስን ለማጎልበት የማይተካ ሚና እንዳለው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
''ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ 5ኛ ዙር ሀገር አቀፍ የክለቦች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተጀምሯል።
ርዕሰ መስተዳድሯ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው እንዳሉት፤ የስፖርቱ ዘርፍ ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባለፈ የህዝቦችን አንድነትና አብሮነትን በማጠናከር ረገድ የላቀ ሚና አለው።
በተለይም የቅርጫት ኳስ ስፖርት እንደ ሀገር ረጅም እድሜ ያስቆጠረ የስፖርት አይነት መሆኑን ጠቅሰው የጋምቤላ ክልልም ከሚታወቅባቸው የስፖርት አይነቶች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።
የክልሉ ወጣቶች ያላቸው ተክለ ሰውነትና ለስፖርቱ ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት ጋር ተዳምሮ የቅርጫት ኳስ ስፖርትን የባህል ስፖርት ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ርዕሰ መስተዳድሯ ተናግረዋል።
የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ቱት ጆክ በዚሁ ጊዜ ከክልሉ የወጡ በርካታ ወጣቶች በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ተሳትፈው ክልሉን ብሎም ሃገሪቷን ማስጠራታቸውን ተናግረዋል።
5ኛው ዙር የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ የክለቦች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በጋምቤላ ከተማ መካሄዱ ያለውን እምቅ አቅም አውጥቶ ለመጠቀም እድል የሚሰጥ መሆኑንም አቶ ቱት ተናግረዋል።
ከዛሬ ግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በሚካሄደው አገር አቀፉ የቅርጫት ኳስ ውድድር አራት የሴቶችና አምስት የወንዶች ቡድኖች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ከወጣው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል።
በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ የጋምቤላና የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የሴቶች የቅርጫት ኳስ ቡድኖች ተጫውተው ጋምቤላ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚን 66 ለ 52 በሆነ ውጤት አሸንፏል።