አፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ተግዳሮቶችን ለመፍታት የራሷን መፍትሄዎች በማፍለቅ በብሔራዊ የልማት አጀንዳዋ እያካተተች ትገኛለች - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ተግዳሮቶችን ለመፍታት የራሷን መፍትሄዎች በማፍለቅ በብሔራዊ የልማት አጀንዳዋ እያካተተች ትገኛለች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2018 (ኢዜአ)፦አፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ተግዳሮቶችን ለመፍታት የራሷን መፍትሄዎች በማፍለቅ፣ በብሔራዊ የልማት አጀንዳዋ እያካተተች መሆኑን የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ከበደ ወርቁ ገለጹ።
አዲስ ዓለም አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤ “አፍሪካ በቀዳማይ ልጅነት ሥርዓት ለውጥ የግንባር ቀደምትነት ሚና፤ ከአካባቢያዊ ሞዴሎች ወደ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የማዕከሉ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ከበደ ወርቁ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በታዳጊ ሕፃናት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ማንኛውም ሀገር በመጪው ትውልድ ላይ ሊያደርጋቸው ከሚችላቸው እጅግ አስፈላጊ ኢንቨስትመንቶች አንዱ ነው።
አፍሪካ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ላይ ያሉባትን ተግዳሮቶች ከመጋፈጥ ባለፈ የራሷን መፍትሄዎች እያመነጨች መሆኑንና ጉዳዩን የብሔራዊ ልማት አጀንዳዋ አካል እያደረገችው መሆኑንም ጠቁመዋል።
አዲስ አበባ ይህንን ጉባኤ እንድታስተናግድ የተመረጠችበት ዋና ምክንያት፣ በዘርፉ እያከናወነች ያለው ተግባር አርአያነት ያለው በመሆኑ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ከተማዋ የጤና እና የሥርዓተ-ምግብ አገልግሎቶችን ያካተተ የተቀናጀ ዘርፈ-ብዙ አሠራር መዘርጋቷን ጠቅሰው፤ የቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርት እና የቀን የሕፃናት እንክብካቤ ማዕከላትን በከተማ አቀፍ ስትራቴጂ ተግባራዊ እያደረገች እንደምትገኝም አስረድተዋል።
በተጨማሪም ለሕፃናት ተስማሚ የሆኑ የመጫወቻ ቦታዎችን እና የወላጆች ድጋፍ ፕሮግራሞችን እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል።
የፖለቲካ አመራር ቁርጠኝነት፣ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ የውሳኔ አሰጣጥ፣ የፖሊሲ ትግበራ፣ የሰው ኃይል ግንባታ እንዲሁም ለዘላቂ ሥርዓት የሚውል ፋይናንስና ኢንቨስትመንት የጉባኤው ዋነኛ አጀንዳዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ጉባኤው በተግባራዊ ትምህርት፣ በጠንካራ አጋርነት እና በመንግሥታት መካከል በሚደረግ የልምድ ልውውጥ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም አመልክተዋል።