ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለነገ የተዘጋጀ ትውልድ ለመገንባት በሕግና በፖሊሲ የተደገፉ የቀዳማይ ልጅነት ኢኒሼቲቮችን እየተገበረች ትገኛለች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለነገ የተዘጋጀ ትውልድ ለመገንባት በሕግና በፖሊሲ የተደገፉ የቀዳማይ ልጅነት ኢኒሼቲቮችን እየተገበረች እንደምትገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ዓለም አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤን በይፋ ከፍተዋል።

ኢትዮጵያ በሰው ተኮር የልማት አቅጣጫ ከምትተገብራቸው ሥራዎች መካከል የቀዳማይ ልጅነት መርኃ ግብር አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።


 

መንግሥት ለሕፃናት ሁለንተናዊ ዕድገት እና ጥበቃ በሕግና በፖሊሲ የተደገፉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በ2015 ተሻሽሎ የፀደቀው ሀገር አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ልማት እና ትምህርት የፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲሁም በ2017 የጸደቀውን አጠቃላይ የትምህርት አዋጅ መሠረት በማድረግ ከሠላሳ አምስት ሺህ በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመላው ሀገሪቱ እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል።

በመንግሥት ተቋማት የሕጻናት ማቆያ ማዕከላት ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ የሕፃናትን ደኅንነት ለማሻሻል የሚያስችል ጉልህ ብሔራዊ መርሐ ግብር መጀመሯን አንስተዋል።

በሰቆጣ ቃል ኪዳን አማካኝነት የዐሥራ አምስት ዓመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ከሁለት ዓመት በታች በሆኑ ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን መቀንጨር በ2022 ዓ.ም ዜሮ ለማድረግ እየተሠራ ሲሆን የሌማት ትሩፋትና የአልሚ ምግቦች ምርታማነት ለስኬቱ ሚናቸው የላቀ ነው ብለዋል።

በተለይም የሕጻናትን ጉዳት ለመቀነስና የልጆችን ጤናማነት ለመጨመር እያስቻሉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ለዘላቂ የልማት ግቦች እና ለሕጻናት መብቶች ጥበቃ የገባቻቸውን ቃል ኪዳኖች ወደ ተግባር እየለወጠች መሆኑን በማንሳት፤ ይህንንም አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቁመዋል። 


 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አመራሩ በወሰደው ቁርጠኝነት፣ በሕፃናት ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ያተኮሩ ስትራቴጂያዊ ኢኒሼቲቮች ተቀርፀው በተግባር ላይ እየዋሉ እንደሚገኙም አስረድተዋል።

ይሕ ወሳኝ የትውልድ ግንባታ ሥራ በአዲስ አበባ ከተማ ፋና ወጊነት ተጀምሮ በመላ ሀገሪቱ እየተስፋፋ መሆኑንም ጠቁመዋል።

መንግሥት ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተቀናጀ የቀዳማይ ልጅነት ልማትን በመላ ሀገሪቱ ለማስፋት ሙሉ ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

አስፈላጊውን በጀት በመመደብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል፣ የተማሪዎችን ምገባ በማስፋፋት ረገድ ውጤት ማምጣቱንም ጠቅሰዋል።

ልጆች በአካልና በመንፈስ የሚጎለብቱባቸው የስፖርትና የመዝናኛ ቦታዎች በየአካባቢው በመገንባት፣ በኮሪደር ልማት ለልጆች ምቹ ሥፍራ እየተፈጠረ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ልጆች ላይ መሥራት ማለት በነገ ሀገር፣ አህጉር እና ዓለማችን ላይ መሥራት በመሆኑ በትጋት ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም