ቀጥታ፡

በክልሉ ያሉ ጸጋዎችን ለይቶ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተሰሩ ስራዎች ስኬታማ ናቸው

ቦንጋ፤ግንቦት 3/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያሉ ጸጋዎችን ለይቶ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተሰሩ ስራዎች ስኬታማ መሆናቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለሕዝብ ተወካዮች እና ለክልል ምክር ቤቶች በብልፅግና ፓርቲ ከቀረቡ ዕጩዎች ጋር የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ በብልጽግና ፓርቲ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክልሉ ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በተሰራው የተቀናጀ ስራ ስኬት መመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ ያሉ ጸጋዎችን ለይቶ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተሰሩ ስራዎች ስኬታማ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ ከማድረግም ባለፈ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመጀመር ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም በመንገድ፣በድልድይና በሌሎችም መሰረተ ልማቶች ውጤት መመዝገቡን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ዘርፍ በትምህርትና በጤና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ውጤቶች መመዝገባቸውንም ተናግረዋል።

መድረኩ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ፍትሀዊና ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ እንዲሁም ተልዕኮዎቹን ለማላቅና የጋራ ዓላማ ለመያዝም የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው፥ ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት ትልልቅ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን ሲያስፈፅምና ሲፈፅም መቆየቱን ገልፀዋል።


 

ለውጡን ለማስረፅና ለማፅናት እንዲሁም የብልፅግና ጉዞን ለማሳለጥ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል ያሉት አቶ ፍቅሬ፥ በሂደቱም በርካታ ሪፎርሞችን በመተግበር ውጤታማ መሆን ተችሏል ብለዋል።

የክልሉ ሕዝቦች የዘመናት ጥያቄ ሆኖ የቆየው በክልል መደራጀት ምላሽ ካገኘበት ማግስት ጀምሮ በፖለቲካዊ፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በተመዘገቡ ውጤቶች የህዝቡ ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ መምጣቱንም ተናግረዋል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እንዲሆን በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በመድረኩ ባለፉት አምስት ዓመታት በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች የተሰሩ ስራዎችና የተመዘገቡ ውጤቶች ላይ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም