ቀጥታ፡

ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን እየተወጣን ነው- ተፎካካሪ ፓርቲዎች 

ደሴ ፤ ግንቦት 3/2018 (ኢዜአ)፦7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለፁ።

ጠቅላላ ምርጫው የህዝብ ተሳትፎ የተረጋገጠበትና ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ለአባላትና ለደጋፊዎቻቸው ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ የምርጫ ህጉን ተከትለው እንዲሰሩ ማድረጋቸውን ፓርቲዎቹ ገልጸዋል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ያላቸውን የፖሊሲ አማራጮች ከማስተዋወቅ ባለፈ ዴሞክራሲያዊ ሥርአቱ እየጎለበተ እንዲመጣ  ለሀሳብ የበላይነት እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የወሎ ህዝቦች ዴሞክራሲ ፓርቲ የምርጫና ዴሞክራሲ ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ የሺበር ጌጡ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፓርቲውን አማራጭ ሀሳብ ለህዝብ እያስተዋወቁ ነው።

በምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ሆነ በምርጫው እለት አባሎቻቸውም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው የምርጫ ህግን እንዲከተሉ በማድረግ ለምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊነት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተፈጠረው ምቹ ምህዳር ህብረተሰቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የፖሊሲ አማራጭና ራዕይ ተረድቶ የሚፈልገውን ፓርቲ  መምረጥ የሚችልበት አውድ ለመፍጠር ማስቻሉንም ገልጸዋል።

"የሰላም ለኢትየጵያ ጥምር ፓርቲ" የምርጫና የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊና የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ፕሬዚዳንት አቶ አላምረው ይርዳው እንዳሉት፤ በጠቅላላ ምርጫው ፓርቲያቸው ሰላምና ልማትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለህዝብ በተለያየ መንገድ አስተዋውቋል።    

በምርጫው ጠንካራ ፉክክርና ክርክር ከማድረግ ባለፈ ተዓማኒ፣ ሰላማዊና አሳታፊ እንዲሆን አበክረው እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ምርጫ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት አንዱና ወሳኝ በመሆኑ በሀሳብ የበላይነት ለማሸነፍ እየተወዳደሩ መሆናቸውን ያነሱት ደግሞ የአንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የቦርድ አባል አቶ ዮሴፍ አሻግሬ ናቸው።

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው የድርሻቸውን እንዲወጡ የማስገንዝብ ሥራ መስራታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም