ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ የጤናውን ሥርዓት በማዘመን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ የጤናውን ሥርዓት በማዘመን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

የጤና ሚኒስቴር ከግንቦት 3 እስከ 7/2018 ዓ.ም በጤና መረጃና ''በዲጂታል ጤና ፈጠራዎች ላይ ዘላቂ ኢንቨስትመንት በማድረግ የጤና ትሩፋቶችን ማሳደግ'' በሚል መሪ ሃሳብ 5ኛው ሀገር አቀፍ የጤና መረጃና ዲጂታል ጤና ሳምንት መርሃ ግብር እያካሄደ ይገኛል።

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የጤና ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች፣ የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲና የሙያና ሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ በጤና ዘርፍ የመረጃ ስርዓትን የሚያዘምን መሰረት ተጥሏል ብለዋል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም የጤና ዲጂታል ሥርዓትን የማጠናከር ሥራ ትኩረት እንደሚሰጠው ገልጸዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓት የጤናውን ዘርፍ በማዘመን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።

በጤናው ዘርፍ በትኩረት ከሚሰራባቸው አምስት ምሰሶዎች መካከል የመረጃ ስርዓት አንዱ መሆኑንም አንስተዋል።

ጠንካራ የጤና መረጃና ዲጂታል ጤና ለዘርፉ አፈጻጸምና ለሕብረተሰብ ጤና  መሻሻል ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ሁሉን አቀፍ የጤና ስርዓት ለመዘርጋትና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ዲጂታል ጤና ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

የዲጂታል ጤና አበረታች ውጤቶች አስመዝግቧል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ከ47 በላይ የዲጂታል ጤና መሳሪያዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ሥራ ላይ እየዋሉ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ከ3 ሺህ 500 በላይ የጤና ተቋማት በኸልዝ ኔት መገናኘታቸውንና ከ227 በላይ ተቋማት የታካሚዎችን መረጃ በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት የማካተት ሥራ በሙሉ ተግባራዊ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ለጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲሁም ስታርታፖችን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በተጠናከረና በታቀደ መልኩ ማሳተፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲዎችም በሰው ሃብት ልማት፣ ምርምርና ፈጠራዎችን በማበረታታት ገንቢ ሚና በመወጣት የመረጃና ዲጂታል ጤና እንዲጠናከር መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

5ኛው ሀገር አቀፍ የጤና መረጃና ዲጂታል ጤና ሳምንት መርሃ ግብርም ለጤናው ዘርፍ ቀጣይነት ያለው የዲጂታል ለውጥ ሚና ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም