የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ግንቦት 3/2018 (ኢዜአ)፡-73ኛው የታላቁ የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም (GHACOF 73) ግንቦት 10 እና 11 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይደረጋል።
ፎረሙ የሚካሄደው “የአየር ንብረት አገልግሎቶች፤ ለአይበገሬነት እና ዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና የመተግበሪያ ማዕከል(ICPAC) ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን ፎረሙን እንዳዘጋጀው ተገልጿል።
ስብሰባው ትንበያ ከመስጠት ባለፈ ትንበያዎቹን ወደ ተግባር መቀየር እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የቅድመ ማስጠንቀቂያና ቅድመ ዝግጅት እርምጃዎችን ማጠናከርን ያለመ ነው።
የአየር ንብረት መረጃዎች አርሶ አደሮች ፣ የጤና ባለሙያዎችን እና የአደጋ ስጋት አመራሮችን በቀጥታ እንዲደግፉ ማድረግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክክር እንደሚደረግ ኢጋድ ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።
በብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር ሌላኛው የመወያያ አጀንዳ ነው።
መድረኩ ለታላቁ የአፍሪካ ቀንድ ግብርና እና የውሃ ሀብት ወሳኝ የሆነውን ከእ.አ.አ ከጁን እስከ ሴፕቴምበር 2026 ያለውን የዝናብ ወቅት ትንበያ ይቀርብበታል።
ሚኒስትሮች፣ የምርምር ተቋማት፣ ሰብአዊ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማህበራት እና የግል ባለሀብቶች ይሳተፋሉ።ይህ የተሳታፊዎች ስብጥር ሳይንስን ከፖሊሲ ጋር ለማገናኘት የታለመ ነው።
የአየር ንብረት መዛባት የሩቅ ስጋት መሆኑ ቀርቶ በደጃፋችን ላይ ያለ ተጨባጭ አደጋ ነው ያለው ኢጋድ ፎረሙ በታላቁ የአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ማህበረሰቦች በቂ መረጃ እንዲኖራቸውና አስቀድመው ዝግጁ እንዲሆኑ ማስቻል ላይ ትኩረቱን ያደረገ መሆኑን አመልክቷል።