የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 31ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 31ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ31ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ነገሌ አርሲ ከድሬዳዋ ከተማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ነገሌ አርሲ በ48 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። ድሬዳዋ ከተማ በ34 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ በ30ኛ ሳምንት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን 2 ለ 1 በመርታት ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል።
ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ከድል ርቋል።
ነገሌ አርሲ ካሸነፈ ተከታታይ ድሉን የሚያስመዘግብ ሲሆን ሁለተኛ ደረጃን የመያዝ እና ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ዝቅ የማድረግ እድልም ያገኛል።
ድሬዳዋ ከተማ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት እና ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ሶስት ነጥብ ማግኘት ይኖርበታል።
ሁለቱ ቡድኖች ዘንድሮ በ12ኛ ሳምንት ባደረጉት ጨዋታ ነገሌ አርሲ 3 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ሀቢብ ከማል፣ ናትናኤል ሰለሞን እና አለኝታ ማርቆስ በወቅቱ ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።
የወቅቱ የሊጉ የዋንጫ ባለቤት ኢትዮጵያ መድን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታውን ያደርጋል።
ኢትዮጵያ መድን በ37 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል። የ2016 ዓ.ም የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ38 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
መድን ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ድል ቀንቶታል። ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ30ኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን 2 ለ 0 አሸንፏል።
ሁለቱም ቡድኖች በድል ጉዟቸው ለመቀጠል ይፋለማሉ።
ቡድኖቹ በመጀመሪያው ዙር በ12ኛ ሳምንት ተገናኝተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2 ለ 1 ማሸነፉ አይዘነጋም።
ናትናኤል ዳንኤል እና አዲስ ግደይ የማሸነፊያ ግቦቹን በወቅቱ ከመረብ ላይ አሳርፈዋል። ረመዳን የሱፍ ለኢትዮጵያ መድን ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሯል።