ቀጥታ፡

የፊዚዮቴራፒ ሕክምና አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀና ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆን እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2018 (ኢዜአ)፦የፊዚዮቴራፒ ሕክምና አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በጤና ሚኒስቴር የስፔሻሊቲና ተሃድሶ አገልግሎት ዴስክ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ሙላቱ ገለጹ፡፡

የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ፊዚዮቴራፒ አሶሴሽን ጋር በመተባበር "የተሃድሶ ሕክምና አገልግሎትን ወደ ማህበረሰቡ እንውሰድ" በሚል መሪ ሐሳብ 23ኛውን ዓመታዊ የፊዚዮቴራፒ ኮንፈረንስ አካሂዷል። 


 

በጤና ሚኒስቴር የስፔሻሊቲና ተሃድሶ አገልግሎት ዴስክ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ሙላቱ፤ የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት ከዋና ዋናዎቹ የቴራፒ ሕክምና ዘርፎች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። 

ይሁን እንጂ ልማዳዊ የፊዚዮቴራፒ ልምዶች እና ከደረጃ በታች የሚሰጡ አገልግሎቶች ለዘርፉ ትልቅ ተግዳሮት መሆናቸውን ጠቁመዋል። 

አሰራሩን ስርዓት ለማስያዝና ለማዘመን ደረጃቸውን የጠበቁ መመሪያዎችና መስፈርቶች እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል። 

ይህም ብቁ ባለሙያዎችን ከማፍራት በተጨማሪ፣ ጥራቱ የተረጋገጠ የተሟላ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ያግዛል ብለዋል። 

ለአምስት ዓመት የተዘጋጀውን ስትራቴጂ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ለማጣጣም የመከለስ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህ ስራ ውጤታማነትም አጋር ድርጅቶች የበኩላቸውን እገዛ እያበረከቱ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ፊዚዮቴራፒ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ዮሃና ጂቫኒ በበኩላቸው፤ ፊዚዮቴራፒ ከአካል ጉዳትና ከተለያዩ ህመሞች ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ለማከም የሚሰጥ ወሳኝ አገልግሎት መሆኑን አስረድተዋል።

በሀገራችን የአገልግሎት ፈላጊው ቁጥርና የባለሙያዎች ብዛት ተመጣጣኝ አለመሆኑን ጠቅሰው አሶሴሽኑ የባለሙያዎችን ብቃትና ክህሎት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲያፈሩ የማገዝ ስራዎችን ጨምሮ የተለያዩ አቅም ግንባታ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም በጎንደር፣ ባህርዳር፣ ጅማና መቐሌ ዩኒቨርሲቲዎች የፊዚዮቴራፒ ትምህርት መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአቤት ሆስፒታል የፊዚዮቴራፒ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ኤክስፐርት ሌንጮ መኮንን እንደገለጹት፤ እንደ ስኳርና ደም ግፊት ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንዲሁም በትራፊክ አደጋ ምክንያት የአገልግሎቱ ፈላጊዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። 

በመሆኑም የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑን አሳስበዋል።


 

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሪሃቢሊቴሽን መምህር በሪሁን አሠፋ በበኩላቸው፣ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የሕክምና ተቋማት ድረስ የተሳለጠ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም