ቀጥታ፡

ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻችንን እንወጣለን- የምስራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎች ሴቶች

ድሬደዋ ፣ ግንቦት 2/2018(ኢዜአ):- የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች ሴቶች አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን  ለምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች ሴቶች በድሬደዋ ያዘጋጀው የምርጫ ታዛቢነት የአሰልጣኞች ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።

በስልጠናው ላይ የተሳተፉት የድሬደዋ አስተዳደር፣ የሐረሪ እና የሶማሌ ክልሎች ሴቶች ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ለሁለት ቀናት የተሰጣቸው ስልጠና በዘንድሮ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የተጣለባቸው የታዛቢነት ኃላፊነት በላቀ ብቃት ለመወጣት ያስችላቸዋል።

ከሶማሌ ክልል ጅግጅጋ የተሳተፉት ወይዘሮ ከድራ ኢብራሂም እንደተናገሩት፤ የዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ታአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየሰሩ ናቸው።

በተለይም በምርጫው የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና የውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲጎለብት እየሰሩ መሆኑን በመግለፅ።

ለሁለት ቀናት የተሰጠን የምርጫ ታዛቢነት የአሰልጣኞች ስልጠና በምርጫው ያለብንን ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ያስችለናል ያሉት ደግሞ ከሐረሪ ክልል ሴቶች ፌደሬሽን የተሳተፉት ወይዘሮ ነጃሃ ኡመር ናቸው።

የቀሰምነውን ዕውቀት በየክልሎቻችን ለሚገኙ የምርጫ ታዛቢ ሴቶች በማካፈል በጠቅላላው ምርጫ ህግና ደንብ በአግባቡ እንዲተገበር የድርሻችንን ኃላፊነት  ለመወጣት ያስችለናል ብለዋል።

ከድሬደዋ አስተዳደር የሴቶች ፌዴሬሽን  የተሳተፉት ወይዘሮ ቅድስት አየለ በበኩላቸው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሴቶች በመራጭነት፣ በተመራጭነት እና በታዛቢነት በመሳተፍ ምርጫው በህዝብ ዘንድ ቅቡል እና ፍፁም ታአማኒ ሆኖ እንዲካሄድ የተቀናጀ ስራ መሰራቱን አስታውቀዋል።

በአስተዳደሩ በምርጫ ታዛቢነት የሚሳተፉ ሴቶች የታዛቢነት መብትና ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲገነዘቡ መደረጉ ኃላፊነትን በትክክል ለመወጣት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል ።


 

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ትዕግሥት ተረፈ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና የውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲጎለብት ውጤታማ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ፌዴሬሽኑ በሀገሪቱ በሁሉም አቅጣጫዎች የሚገኙ ሴቶች በሁሉም መስክ ተሳትፏቸው እንዲጨምር መስራቱን ጠቅሰው በፌዴሬሽኑ በ54 የተለያዩ አደረጃጀቶች የታቀፉ ሴቶች አባላቱ በምርጫው የላቀ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን  አንስተዋል።

በዘንድሮ ምርጫ ላይ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ 10 ሺህ ሴቶች ነፃ እና ገለልተኛ ሆነው  በታዛቢነት ይሳተፋሉ ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም